በአዲስ አበባ ብቻ ዋጋ ጨምራችሁዋል በሚል ከ 4 ሺ በላይ ሱቆች ታሸጉ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 05 ቀን 2010 ዓ/ም) የአዲስ አበባ መስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊን ጠቅሶ ሪፖርተር እንደዘገበው የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል የተባሉ 4 ሺ 22 ሱቆች የታሸጉ ሲሆን፣ 7 ሺ ሱቆች የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ 8 ሺ የሚሆኑት ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። የዋጋ ጭማሪው ከውጭ ምንዛሬ እጥረትና ከአቅርቦት እጥረት ጋር የተያያዘ ሆኖ ሳለ እርምጃው በነጋዴዎች ላይ መወሰዱ አግባብ አለመሆኑን ነጋዴዎች ይገልጻሉ።
በመዲናዋ የዋጋ ውድነቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሰሞኑን አስታውቆ ነበር። በየካቲት ወር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ካሳዩት የግብርና ምርቶች መካከል በርበሬ፣ ጤፍ እና የወጥ እህል ይገኙበታል። ጤፍ በኩንታል እስከ 3300 ብር፣ በርበሬ በኪሎ እስከ 150 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ምስር እስከ 40 ብር፣ዘይት ደግሞ በሊትር 90 ብር በመሸጥ ላይ ነው። ስኳር ግን ጨርሶ ከገበያ መጥፋቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ሸማቾች በእየለቱ በሚንረው የዋጋ ጭማሪ ድንጋጤ ውስጥ እንደገቡ እየገለጹ ነው።
ካለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ የሚካሄደው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። የስራ ማቆም አድማዎች የትራንስፖርት መስተጓጎል መፍጠራቸው፣ ፋብሪካዎች በአድማዎች ምክንያት በየጊዜው ስራ ማቆማቸው፣ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ በባንክ እንዳይልኩ ጥሪ ማቅረባቸው፣ የቱሪዝም ፍሰት መቀነሱና ወደ ውጭ የሚላከው ምርትና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ማሽቆልቆሉ፣ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው።