መጋቢት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ውስጥና በዙሪያዋ ዋና መግቢያ በሮች በሚገኙ ከተሞች በየቀኑ የሚከሰተውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የትራፊክ አደጋ ተከትሎ በአንድ ክፍለ ከተማ ብቻ 3 ሰዎች በየቀኑ እንደሚሞቱ ለማዎቅ ተችሏል፡፡
በረ/ኢ/ር አሰፋ መዝገቡ በኩል ከመንግስት ሚዲያዎች በየቀኑ እንደሚገለጸው በከተማዋ የሚከሰተው የትራፊክ አደጋ ቁጥር ከመቼውም በተለየ እየጨመረ ሲሆን ለዚህም እንደምክንያት የሚቀርበው ለመንገደኛ ቅድሚያ መከልከል፣ርቀትን ጠብቆ አለማሽከርከር፣ቁም የሚል ምልከት አልፎ መሄድ፣ የአሽከርካሪ ብቃት ማነስ፣ወደ ግራና ቀኝ ያለጥንቃቄ መታጠፍ፣ርቀትን ጠብቆ አለማሽከርከር ናቸው።
ይሁን እንጅ በቅርቡ የተደረጉት ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ከመቼውም በተለየ አኳኋን እየተካሄ ባለው ሰሞነኛ የዘመቻ ግንባታ ማለትም የቤቶች፣የመኪና መንገድና የባቡር መንገድ ስራዎች በርካታ ዜጎች በመኪና እንዲገጩ ምክንያት እየሆነ ነው።
ዋና የመኪና መንገዶች ለዕድሳት በሚል እየፈራረሱ በአጥር መታጠራቸው፣ በየአካባቢው ለግንባታ ግብዓት አቅርቦት በሚል በአሸዋና ድንጋይ ክምር መዘጋታቸው፣ በመንገድና በድልድይ ፍርስራሾች ማስተንፈሻ አማራጭ መንገዶች ሳይቀሩ መዘጋታቸው፣ ለግንባታ ሂደት የሚያግዙ አዳዲስና አሮጌ ከባድ የጭነት መኪኖች ለረጂም ሰዓታት ሲቆሙ መንገዶች መጨናነቃቸው፣ ማስተንፈሻ ተብለው የተመደቡ መሿለኪያ መንገዶች የሚገኙት በነዋሪዎች ሰፈር በመሆኑና ስፋታቸው አነስተኛ መሆኑ የከተማው ተሸከርካሪዎች ባሉበት መንገድ ላይ ለረጅም ሰዓት መኪኖች እስከሚያልፉ ለመቆም በመገደድ ነዋሪዎቹ ለአደጋ ይጋለጣሉ።
የአዲስ አበባ ብዙ መንገዶች ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ እየተዘጉ ነው። በመኖሪያ ሰፈር ስር ባሉ ጠባብ መሿለኪያ መንገዶች ሰውና መኪኖች የሚጋፉባት፣ ድንገት በሚንሻራተቱና በሚናዱ መንገዶች ከቀላል እስከ ከባድ መኪና የሚጓዙባትና መኪና በየጊዜው የሚገለበጥባት፣ ጠባብ ድልድዮች ላይ መኪኖች ተደርበው የሚያልፉባት፣ በድንገት የመኪና ብልሽት አጋጥሞ መኪና ከቆመ አንድ መንገድ ላይ ተቆሞ የሚዋልባት ከተማ ሆናለች።
በከተማዋ የሚገኙት ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች በብቃት መመዘኛ በዓለም ገበያ ላይ ምርታቸው የቆመ፣ ከተበላሹ መለዋወጫ የሌላቸው፣በብቃት ማነስ በየቦታው አደጋ የሚያደርሱ፣ ያለ በቂ ፍተሻ ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ፣ የብቃት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ ናቸው፡፡
በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ መስተዳድሩ እርምጃ እየወሰድኩ ነው ቢልም እስካሁን አርኪ ውጤት ሊገኝ አልቻለም።