ግንቦት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፌዴራል የሥነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሸን በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን (ኮንዶሚኒየም) ለባለዕድለኞች የማሰተላለፍ ሒደት ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጠ መሆኑን በጥናት ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡
ኮሚሸኑ ያካሄደውና በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው በከተማዋ ዲዛይንና አስተዳደር ልማት ቢሮ ካሉበት ለሙስና የተጋለጡ ችግሮች መካከል ቤቱን ትክክለኛነቱን አረጋግጦ በመፈራረም አያሰረክብም የሚለው ይገኝበታል፡፡
ኮሚሸኑ በጥናቱ እንደአብነት ካነሳው ውስጥ በልደታ ፣በአራዳና በቂርቆስ ክ/ከተሞች ከባለዕድለኞች ጋር የቤት ርክክብ የሚደረገው እማኞችን ይዞ በመቅረብ ወይም ከክ/ከተማ ቤት ማሰተላለፍና አስተዳደር ንዑስ የሥራ ሒደት ባለሙያዎችን እማኞች በማድረግ ሲሆን ቁልፍ ላልተዘጋጀላቸው ቤቶች ደግሞ ቤቱ ለሚገኝበት አካባቢ ኮንዶሚኒየም ማኀበር ተጠቃሚው ቤቱን ሰብሮ እንዲገባ የተፈቀደለት መሆኑን የሚያሳይ ደብዳቤ እንደሚጽፉና ተጠቃሚው ደብዳቤውን በማሳየት ሰብሮ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል ይላል፡፡
ይህ ዓይነቱ አሰራር ባለዕድለኞች የደረሳቸውን ቤት በቀላሉ እንዳያገኙና እንዲጉላሉ ከማድረግ አልፎ ከተሰጣቸው ቤት ውጪ ወደ ሌላ ቤት እንዲገቡ መንገድ በማመቻቸት ከተጠቃሚው ጋር አለመግባባት እንዲፈጠርና ኀ/ሰቡ ላልተገባ ተግባር የሚጋብዝ አሰራር መሆኑ ተረጋግጧል ብሏል፡፡
በተመዝጋቢዎች የመዝገብ ቁጥር ላይ የሌላ ግለሰብ ሰም እንደሚመዘገብም ኮሚሸኑ አጋልጧል፡፡ከዚሁ ጋር ተያይዞም ተመዝጋቢዎች ስለመዝገባቸው የሚያውቁበት ሥርዓት ያልተዘረጋና በመረጃ ቋት( ዳታ ቤዝ) ላይ ያለው መረጃ እንዳይለወጥ ወይም እንዳይነካ የሚያደርግ የውስጥ ክትትልና ቁጥጥር ባለመኖሩ በአንድ ተመዝጋቢ ቁጥር ላይ የሌላ ግለሰብ ሰም ተመዝግቦ የመገኘት ሁኔታ እንዳለ ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡በመሆኑም በወቅቱ የተመዘገቡና ከዛሬ ነገ ዕጣ ይወጣልኛል ብለው የሚጠባበቁ ሰዎች በድርድር ፣በመመሳጠር ተወግደው በሌሎች የሚተኩበት ሁኔታ መፈጠሩን የኮሚሸኑ ጥናት ያሳያል፡፡
የግል ቤት ያላቸው፣በቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በዕጣ ኮንዶሚኒየም ቤት ወስደው አከራይተው የሚጠቀሙበት ሁኔታ መኖሩን፣አስተዳደሩ ይህንን ተከታትሎ ለማሰቆም እንዳልቻለ ያትታል፡፡ሌላው ቀርቶ በአራዳ ክ/ከተማ ለሸራተን ማሰፋፊያ ፣በቂርቆስ ክ/ከተማ የልማት ተነሺዎች እንዲሁም በልደታ ክ/ከተማ ከቀድሞ 39/49 እና 53 ተነስተው ምትክ ቤት ያገኙ ሰዎች ቤት ለመውሰድ ከሚጠባበቁ የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ዝርዝር ውስጥ ስማቸው እንዳልተሰረዘ በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡
ከምርጫ 97 በሁዋላ የህወሀት አባላት በአዲስ አበባና በሌሎች ታላላቅ ከተሞች የሚገኙ ቁልፍ ቦታዎችን እንዲሁም የኮንዶሚኒየም ቤቶችን መቆጣጠራቸው ይታወሳል። አብዛኛው የህወሀት ወታደሮች ከአንድ በላይ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በመያዝ እና በማከራየት ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኙ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።
በአዲስ አበባ በ1996 ዓ.ም የቤቶች ልማት ፕሮግራም ሲጀመር ከ350 ሺ በላይ ሕዝብ የኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት ተመዝግቦ ከዛሬ ነገ ዕጣ ይደርሰኛል በሚል የሚጠባበቅ ነው፡፡ባለፉት ስምንት ዓመታት ለባለዕድለኞች የተላለፉ ቤቶች ቁጥር 63 ሺ 677 ያህል ሲሆን በአሁኑ አካሄድ ከቀጠለ ተመዝጋቢውን ብቻ ለማዳረስ ከ20 ዓመታት በላይ ግዜን ይወሰዳል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide