በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት ሁለት የተቃዋሚ ፓርተዎች አባላትን አፍነው ወሰዱ

ግንቦት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢሳት የደባርቅ ወኪል ባስተላለፈው መረጃ መሰረት በትናንትናው እለት ቀድሞ የመኢአድ አባል የነበረውና በምርጫ 97 ቅንጅትን፣ በምርጫ 2002 ደግሞ አንድነት ፓርቲን በመወከል ሲንቀሳቀስ የነበረውን አቶ ስለሺ ጥጋቤን አፍነው ወስደውታል።

ግለሰቡ ከተያዘ በሁዋላ ቤቱ ለ2 ሰአታት ሲበረበር እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል።  የአቶ ስለሺ ጥጋቤ ቤተሰቦች ለኢሳት እንደገለጡት፣ ፖሊሶች እና የደህንነት ሰዎች ግለሰቡን አፍነው ወደ አዲስ አበባ ወስደውታል።

በጭልጋ ወረዳ ደግሞ የመኢአድ አደራጅ የሆነው አቶ መለሰ አስሬ ትናንት ቤቱ ሲፈተሽ ከቆየ በሁዋላ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስዷል።

ግለሰቦቹ ታፍነው ስለተወሰዱበት ምክንያት እና የት እንዳሉ የታወቀ ነገር የለም። አንድነት ፓርቲም ሆነ መንግስት በግለሰቦቹ መታሰር ዙሪያ የሰጡት አስተያየት የለም።

ይሁን እንጅ ዘጋቢያችን እንደሚለው ከዋልድባ ገዳም እና ከራስ ዳሸን  ጋር በተያያዘ በአካባቢው ከሚታየው ውጥረት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። የደባርቅ ወረዳ ወጣቶች ከዋልድባ፣ ከራስ ደጀን እንደሁም ከመልካም አስተዳዳርና ፍትህ እጦት ጋር በተያያዘ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በተደጋጋሚ እንደሚላተሙ ይታወቃል። የደባርቅ መምህራን የደሞዝ ጭማሪ ይደረግልን በማለት ተቃውሞ ካሰሙ መምህራን መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። በጭልጋ ወረዳም እንዲሁም መምህራን የስራ ማቆም እድማ ማድረጋቸው ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide