በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአውሮፓ ህብረት ጽህፈት ቤት ፊትለፊት የተቃውሞ ሰልፍ ሊያደርጉ ነው

ግንቦት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያውያን ማህበር በኔዘርላንድስ ከቤልጂየም የኢትዮጵያውያን ማህበር ጋር በመተባበር የፊታችን ረቡእ ፣ እኤአ ሜይ 15፣ 2013 በብራሰልስ በሚገኘው በአውሮፓ ህብረት ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርግ ለኢሳት በላከው ደብዳቤ አስታውቋል።

 

ሰልፉ በአማራ ተወላጆች ላይ በተደጋገሚ እየተፈጸመ ያለውን የማፈናቀል ዘመቻ ፣ በልማት ስም የአፋር፣ የጋምቤላ እና የሌውንም ህዝብ ህልውና ለማጥፋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማውገዝ፣ በየእስር ቤቱ ውስጥ በመሰቃየት ላይ የሚገኙ የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ ለመጠየቅ፣ እንዲሁም በክርስቲያኑና በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ የሚያደርገውን የመከፋፈል ዘመቻና ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም ይጠይቃል።

 

ማህበሩ በሰልፉ ላይ በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲገኙ እና ለወገኖቻቸው ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ በተለያዩ ክፍለ አለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እያወገዙት ይገኛል።