በአወልያ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው

ሐምሌ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአወልያ የተጀመረው ተቃውሞ በትናንትናው እለት ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ ከ5 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን ዘጋቢዎቻችን ገልጠዋል ። መንግስት የቆሰሉ እንጅ የሞቱ ሰዎች የለም ይላል። የሙስሊሙ ኮሚቴ አንድ ሰው እንደተገደለ ለብሉምበርግ ገልጧል። ኢሳት የማቾችን ቁጥር ከሌሎች ገልተኛ ወገኖች አግኝቶ ለማረጋገጥ አልቻለም።

ሌሊት በጥይት የተመቱ ሰዎች በመጀመሪያ ወዸ ጰውሎስ ሆስፐታል፣ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስቲታል ተወስደዋል።

ትናንት ማታ በጅምላ በቁጥጥር ስር ውለው ወደ አራዳ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩት ሰዎች መካከል ፣ ዜናውን እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ 16 ሰዎች ቀርተው ሌሎች ተለቀዋል።  ነገር ግን በኮልፌ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩት ሴቶች ውስጥ እንዲሁም ወደ አልታወቁ ቦታዎች ከተወሰዱት ወጣቶች መካከለ ምን ያክል ሰዎች እንደተፈቱ አልታወቀም።

በአሁኑ ጊዜ በአስር  ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በአንዋር መስኪድ ተሰባስበው አሉዋ ክበር እያሉ ተቃውሞአቸውን እየገለጡ ነው።

ፍጥጫው የተጀመረው፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በትናንት ምሽት የ 2፡00 ሰዓት ዜና እወጃው፤ ሙስሊሙ ህብረተሰብ እያደረገ ያለውን ሰላማዊ ተቃውሞ የሚኮንን ዜና  ማቅረቡን ተከትሎ ነው።

ኢቲቪ ስለሙስሊሙ ህብረተሰብ  እንቅስቃሴ ባስራጨው  በምሽት ዜናው፤ በተቃውሞ ላይ ያሉት ሙስሊሞች፤ ለነገ ሐምሌ ስምንት ቀን የጠሩት የሰደቃ እና የአንድነት ፕሮግራም፤ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ለማደናቀፍ ሆነ ተብሎ የተጠራ መሆኑን  በመጥቀስ እና እስከዛሬ በየመስጊዱ የሚደረገው ተቃውሞ፤ “ሰላማዊ ሳይሆን የሀይማኖት አባቶች የተደበደቡበት እና በፖሊስ ላይ ትንኮሳ የተደረገበት” እንደነበር በማብራራት፤ “ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከዚህ ተግባሩ ባስቸኳይ እንዲቆጠብ!” የሚል  መልዕክት አስተላለፈ።
ይህንንም ተከትሎ ፤  የሙስሊም ህብረተሰብ  ወኪሎች  በነገው ዕለት ለሚካሄደው የሰደቃ እና የአንድነት ፕሮግራም ማዘጋጂያ እንዲሆኑ በማለት  በአወሊያ ግቢ ያስገቧቸውን ዕቃዎች እንዲያነሱ እና ለዝግጅቱም ምንም አይነት መሰናዶ እንዳያደርጉ የፌዴራል ፖሊስ አስጠነቀቀ።

ከዚያም በማስከተል የፖሊስ አባላት  ወደ አወሊያ ግቢ በመግባት ለሰደቃ ፕሮጋራሙ ቀደም ብለው ተዘጋጅተው የነበሩ እቃዎቹን መበታተን ጀመሩ።

ይህም ዜና ከመቅፅበት  በፌስ ቡክና በድረ ገፆች  ተለቀቀ። ሙስሊሙ ህብረተሰብም ከየአካባቢው፦ “አሏህ ዋክበር” እያለ  ወደ አወሊያ መትመም ጀመረ። በእኩለ ሌሊት የአወሊያ አካባቢ በታጣቂዎች ተኩስ መናወጥ ሲጀምር፤ ከየመስጊዶች ሚናራ የአደጋ ጊዜ የአዛን ጥሪ አስተጋባ።ህዝቡም  ይበልጥ ወደ አወሊያ መጎረፍ በጀመረ።

በአንፃሩ  በተለያዩ አቅጣጫዎች የሰፈሩ በርካታ የፖሊስ አባላት  ህዝቡ ወደ አወሊያ እንዳይሄድ መንገድ ዘግተው በተኩስ እና በዱላ መከላከል ቀጠሉ።ፍጥጫው ወደ ከፋ ሁኔታ ተሸጋገረ። ቀደም ሲል በአወሊያ  በተገኙ ሙስሊሞች ላይ ድብደባ ሲፈፅምና አስለቃሽ ጭስ ሲረጭ የነበረው ፖሊስ፤ ሁዋላ ላይ ወደ ሰው መተኮስ እንደጀመረ  የኢሳት ወኪል አመልክቷል።

የተለያዩ ሚዲያዎችና  ድረ-ገፆች እንደዘገቡት፤ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት በትንሹ አምስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤በርካታዎች ደግሞ ቆስለዋል።አንዳንድ ወገኖች ግን የሟቾችን ቁጥር ከደርዘን በላይ ያደርጉታል።

ይሁንና ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በግጭቱ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።

ከሞቱትና ከቆሰሉት በተጨማሪ፤እጅግ በርካታዎች ደግሞ በጭነት መኪና ታጭቀው ለጊዜው ወዳልታወቀ ቦታ ተግዘዋል።

ወኪላችን ያጠናቀረው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ድርጊቱ ሙስሊሙን ብቻ ሳይሆን ክርስቲያኑን ህብረተሰብ ጭምር ክፉኛ አስቆጥቷል።

በዚያ ሌሊት በቀጥታ ከታጣቂዎች ሲተኮስባቸው የነበሩት ሙስሊሞችን በርካታ ክርስቲያኖች ወደ ቤታቸው በማስገባት  እንዳተረፏቸውም ታውቋል።

ይህ የትብብር መንፈስ ባይኖር ፤ኖሮ የሟቾች ቁጥር እጅግ ያሻቅብ ነበር ተብሏል።

ክርስቲያን ወገኖቿ ባሳዩት ፍቅር ልቧ የተነካ ሜራኑ ሀቢቢቲ የተባለች ሙስሊም፤ በፌስ ቡክ ገጿ ባሰራጨችው ጽሁፍ፦”ትናንት ሌሊት  ሙስሊሞችን- ከጨካኞቹ እና ሰላማዊ ሰው ላይ ተኩስ ሲከፍቱ ከነበሩት ፌዴራሎች ለመከላከል፤እቤታችሁ በማሳደር እና ውሀ በማቀበል ፤ወገናዊ ትብብር ላሳያችሁን ክርስቲያን ወንድሞች፣እህቶች፣እናቶችና አባቶች ከልብ እናመሰግናችሁዋለን!”ብላለች።

ውጥረቱና ፍጥጫው  ዛሬም ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፤“ሰላማዊ እና ህገ-መንግስታዊ ጥያቄያችን በጠመንጃ ሀይል አይቀለበስም” ያሉ ሙስሊሞች፤ በመላ አገሪቱ ያሉ ሙስሊሞች ከዛሬ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአንዋር መስጊድ  ዙሪያ የሚኖሩ ሙስሊሞች ባወጡት የአቋም መግለጫ  ደግሞ ፤”ጥያቄዎቻችን ግልጽና ትክክለኛ ምላሽእስኪያገኙ ድረስ ከዛሬ ጀምሮ ውሎና አዳራችን በአንዋር መስጂድ  ውስጥ ይሆናል” ብለዋል።

በደሴ የሚገኙ ሙስሊሞች በበኩላቸው ፤በአዲስ አበባ ለተጎዱ ወንድሞቻቸው አጋርነታቸውን ለመግለጽ በአንድ ላይ በመሰባሰብ ተቃውሞ ለማሰማት መዘጋጀታቸው ታውቋል።

በሙስሊሞች ላይ የተፈጸመው ጥቃት አስመልክቶ የፖለቲካ ድርጅቶችም የተቃውሞ መግለጫዎችን እያወጡ ነው። ድርጊቱን አጥብቀው ከኮነኑት መካከል የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ አንዱ ነው።

“የ ኢትዮጵያ ወጣቶች ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር የመቆም ታሪካዊ ግዴታ አለብን” በሚል ርዕስ ንቅናቄው ባወጣው በዚሁ  መግለጫው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በ አንድነት በመተባበር በወገን ላይ ያነጣጠረውን የወያኔ ጥፋት በጋራ እንዲመክት ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፤መንግስት የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ እየተካሄደ ባለበት አካባቢ የራሱን ሰዎች በማደራጀት እና ሲረብሹ ቪዲዮ በመቅረጽ ፤የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ከነውጥ ጋር አያይዞ በኢቲቪ ፕሮፓጋንዳ ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑን የውስጥ ምንጮች  አጋልጠዋል።

በሌላ በኩል እጅግ በርካታ ሙስሊሞች ዛሬ ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ እንደወትሮአቸው ለስግደት ሸራተን አዲስ አካባቢ ወደሚገኘው መስጊድ ቢሄዱም፤ “ለአፍሪካ ህብረት ለመጡት እንግዶች ደህንነት ሲባል ወደ መስጊዱ አትገቡም” ተብለው ከፌዴራል ፖሊሶች ጋር ተፋጠው ውለዋል።

ወኪሎቻችን እንዳጠናቀሩት መረጃ፤በአሁኑ ጊዜ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በፌዴራል ፖሊሶችና በወታደሮች ተጨናንቀዋል።

ይህንኑ ተከትሎ የሙስሊሞች ጊዜያዊ ኮሚቴ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ ህዝበ-ሙስሊሙን በመንገድ ላይ በታጣቂዎች እየተፈፀመበት ካለው ትንኮሳ እና ጥቃት ለመከላከል ፤ተቃውሞው በአንዋር መስጊድ እንዲቀጥል መወሰኑን አሳውቋል።

በመሆኑም ሙስሊሞች በመንገድ ላይ የፈሰሱት ታጣቂዎች ቢተናኮሷቸውም ትንኮሳውን በጥንቃቄ በማሳለፍ ቀጥታ ወደ አንዋር መስጊድ እንዲመጡ ጥሪ አቅርቧል።

በዚህም መሰረት  ህዝቡ ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ጊዜ ወደ አንዋር መስጊድ እየተመመ እንደሚገኝ ታውቋል

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide