ጥር 19 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ባለፈው ሳምንት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በመስጊዱ ግቢና ከመስጊዱ ውጭ በመሆን ስግደት ከሰገዱ በሁዋላ የመብት ጥያቄዎችን በመፈክር ካሰሙ በሁዋላ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር ተስማምተው ተለያይተው ነበር።
በዛሬው የጁማ ስግደት ካለፈው ሳምንት የበለጠ ህዝብ የተገኘ ሲሆን፣ የተለያዩ የሙስሊሙ ተወካዮች ንግግር አድርገዋል።
ኡስታዝ ያሲን ኑሩ በዲናችን ( በሀይማኖታችን) አንደራደርም፣ መሞት ካለብንም እንሞታለን ብለው ለተሰብሳቢው መናገራቸውን በስፍራው የነበረው ዘጋቢያችን ገልጧል።
የሀይማኖቱ መሪዎች ለመንግስት የሚቀርቡትን ጥያቄዎች በማዘጋጀት ሙስሊሙ እንዲፈርምበት አድርገዋል።
የኮሚቴው አባላት የተለያዩ የመንግስት አካላትን በማነጋገር የሚያገኙትን መልስ ረቡእ ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ሙስሊሞቹ መንግስት አህባሽን ለማስፋፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ያቁም፣ መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ አይግባ፣ የአወሊያ ኮሌጅ ይከፈት፣ የሙስሊሞች ምክር ቤት ( መጅሊሱ) ፈርሶ ሙስሊሞ የራሱን መሪዎች ራሱ ይምረጥ የሚሉ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ።
የሙስሊሞቹ ጥያቄ በመላ አገሪቱ በተለያዩ ጊዜዎች እንደሚቀጠል የደረሰን መረጃ ያሳያል።
የመንግስት ባለስልጣናት በአወልያ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እስካሁን ድረስ ለማስቆም ሙከራ አላደረጉም።