(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 19/2011)በአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በአምስት የሰሜን አሜሪካ ከተሞች ሕዝባዊ ውይይት እንደሚያካሄድ የዝግጅቱ ኮሚቴ አስተባባሪዎች ገለጹ።
አስተባባሪዎቹ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ሕዝባዊ ውይይቱ የሚካሄደው ስለተጀምሩ ሃገራዊ ለውጦችና ስለ ኢንቨስትመንት ከኢትዮጵያያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ነው።
በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ሕዝባዊ ውይይት የሚያደርግባቸው አምስቱ የአሜሪካ ከተሞች ዋሽንግተን ዲሲ፣ ዳላስ ፣ሲያትል፣ ሎደንጀለስ እና አትላንታ ናቸው ።
በኢትዮጵያ የለውጥ አየር መንፈሱን ተከትሎ በአማራ ክልል ወጣቶች በተከፈለው መስዋዕትነት የቀድሞው ብአዴን የአሁኑ አዴፓ መነቃቃት ጀመረ።
ወትሮ ወትሮ በሕወሃት ተላላኪነት ሲፈረጅ የነበረው ብአዴን ከውስጡ በተገኙ ጥቂት አመራሮች ከስውር አገዛዝ ተላቀው የሕዝቡን ስሜት ማዳመጥ ጀመሩ።
በኢትዮጵያ በኢሕአዴግ ውስጥ ለውጥ እንዲነቃነቅ ምክንያት ከሆኑት አመራሮች መካከል ደግሞ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አንዱ ናቸው።
ከወልቃይትና ከግጨው መሬት እንዲሁም ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አባይ ወልዱ ጋር ብሎም ከሕወሃት ጋር የተናነቁት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና በእሳቸው የሚመራው የብአዴን ቡድን እንደንበር ይነገራል።
በዚሁ ሚና ውስጥ ደግሞ ዋነኛውን የለውጥ ትግል የለኮሱት በቅርቡ ከዚህ አለም የተለዩት አቶ ተስፋዬ ጌታቸውና አሁንም በአመራሩ ውስጥ የሚገኙት ዶክተር አምባቸው መኮንንም ይጠቀሳሉ።
የቀድሞው ብአዴን የአሁኑ አዴፓ ፊታውራሪ አቶ ደመቀ መኮንንም የሕወሃት መልዕክተኞች ከሚባሉት አቶ በረከት ስምኦንና ታደሰ ካሳ እንዲሁም ከሌሎች ለውጥ አደናቃፊዎች ጋር ዋጋ መክፈላቸውም ይነገራል።
እናም በዚሁ ተጋድሏቸው የሚታወቁት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ቡድናቸው የሕዝብ ይሁንታ ማግኘታቸው ግልጽ እየሆነ መጥቷል።
በሕወሃት ደጋፊዎችና አክቲቪስቶች ክፉኛ የሚነቀፉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናትን መርተው ከመጭው እሁድ ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ ሕዝባዊ ውይይት ያካሂዳሉ።
ለዚሁም በመጭው ቅዳሜ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚገቡ ነው የተነገረው።
የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራውና በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚኒስትሪ ካውንስል አቶ ደመቀ ዘመነ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቡድን በ5 የአሜሪካ ግዛቶች ሕዝባዊ ውይይት ያካሂዳል።
በዚሁ ውይይታቸውም ከአማራ ተወላጆችና የአማራ ክልል ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ምክክር ያደርጋሉ።
በተጓዳኝም ከባለሃብቶች ፣ ከምሁራን፣ ከፖለቲከኞችና ከታዋቂ ግለሰቦች ጋር እንደሚገናኙና እንደሚወያዩም ነው የተገለጸው።
እንደ አስተባባሪዎቹ ገለጻ የውይይቱ አጀንዳዎችም ስለ ሃገራዊ ለውጡ የእውቀት ሽግግር ስለማድረግና ኢንቨስትመንት ላይ ያተኩራሉ።
በመጀመሪያ ውይይታቸው ዴሴምበር 2 በእለተ እሁድ ከ1 ፒ ኤም ጀምሮ የቨርጂኒያ፣ሜሪላንድና የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሴሚናሪ ሂልተን ሆቴል ይታደማሉ።
በዚሁም ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ ተነግሯል።
በአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው ቡድን የክልሉ ሕዝብ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ አለመሆኑን፣ ድርጅቱ አዴፓ ለሕወሃት ተገዥ ሆኖ በመቆየቱ በተፈጠረው ችግር ዙሪያም ከተቺዎች ጥያቄዎች ይቀርባሉ ተብሎም ይጠብቃል።