ነሀሴ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከሁለት ሳምንት በፊት አቶ በረከት ስምኦን ፣ የአቶ መለስ ዜናዊ የቀብር ስነስርአት እንደተፈጸመ ፣ የአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ስልጣን ፓርላማው በአስቸኳይ ተጠርቶ ያጸድቀዋል የሚል መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ የመንግስቱ የመገናኛ ብዙሀን አቶ ሀይለማርያምን ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር እያሉ እስከመጥራት ደረሱ። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረትም አቶ ሀይለማርያም እስከ 2007 ዓም የጠቅላይ ሚኒሰትርነቱን ቦታ በመያዝ ስራቸውን እንዲሰሩ ፈቅዷል። አቶ በረከት ብአዴኖች እና ኦህአዴዶች የሚበዙበትን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመጠቀም እንዲተላለፍ ያስደረጉትን ውሳኔ፣ አቶ አባዱላ ገመዳ ተጣድፈው በፓርላማ ለማጸደቅ ሲሩዋሩዋጡ፣ የህወሀት ቡድኖች አካሄዱ ልክ አይደለም የሚል ቅሬታ በማቅረባቸው ጉዳዩ ከቀብር በሁዋላ እንዲታይ ተወሰነ።
ህወሀት በብአዴኑ አቶ በረከት ስምኦንና በኦህዴዱ አባ ዱላ ገመዳ ድርጊት በመበሳጨት ፣ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር የሚሾመው የኢህአዴግ ምክር ቤት እንጅ የሚኒሰትሮች ካውንስል ባለመሆኑ ፣ አቶ ሀይለማርያም በሚኒሰትሮች ምክር ቤት እንደተሾሙ ተደርጎ የሚቀርበው ዘገባ ትክክል አይደለም የሚል መከራከሪያ አቅርቧል። ህወሀት አቶ በረከት ግርግሩን በመጠቀም ህግ ጥሰዋል በሚልም ከፍተኛ ትችት ሲያወርድባቸው ሰንብቷል። ህወሀት አቶ ሀይለማርያም በመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒሰትር እየተባሉ እንዳይጠሩ በሚል ያቀረበውን አቤቱታ ፣ አቶ በረከት በከፍተኛ ደረጃ ቢቃወሙትም፣ እስከመጨረሻው ባለመዝለቃቸው አቶ ሀይለማርያም በድሮው ማእረጋቸው እንዲጠሩ ወስኗል።
በዚህ መሀል ወ/ሮ አዜብ መስፍን አቶ በረከት ስልጣኑን ከህወሀት እጅ ለማውጣት የሄዱበት መንገድ ስለበሳጫቸው፣ ከአቶ በረከት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በማቋረጥ ህወሀትን ለማሰባሰብ ሲደክሙ ሰንብተዋል። አቶ በረከትም ወ/ሮ አዜብ በቀብሩ ስነስርአት ላይ መናገር ያለባቸው መንግስት ጽፎ የሰጣቸውን እንጅ፣ ከራሳቸው መሆን የለበትም በሚል ውሳኔ ጽሁፉን ወ/ሮ ነጻነት አስፋው እንዲጽፉትና ለወ/ሮ አዜብ እንዲሰጡ ቢታዘዙም ፣ ወ/ሮ አዜብ ግን አሻፈረኝ ብለው ” በኢህአዴግ ውስጥ ችግር እየተፈጠረ መምጣቱን የሚጠቁም፣ እርሳቸውም ለስልጣን ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ” ንግግር አቀረቡ።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ በትናንትናው እለት ባደረገው ስብሰባ ፣ የአቶ ሀይለማርያምን ሹመት በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ይሁን እንጅ ክርክሩ ጠቅላይ ሚኒሰትርን የሚሾመው የኢህአዴግ ምክር ቤት ነው ወይስ የሚኒሰትሮች ምክር ቤት በሚል ሲወዛገብ በማምሸት በመጨረሻም፣ ህወሀት የያዘው አቋም አሸናፊ ሆኖ በመውጣት በአቶ በረከት መሪነት በሚኒሰትሮች ምክር ቤት ጸድቆ የነበረው የአቶ ሀይለማርያም ስልጣን ውድቅ እንዲደረግ ወስኗል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ” ዋናው ጉዳይ የሆነው ለህዝቡ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት በቂ ምላሽ መስጠት በሚቻልበት አቅጣጫ ዝግጅት እየተደረገ የግንባሩን ሊቀመንበርና ም/ሊቀ መንበር የመሰየም ጉዳይ የግንባሩ ምክር ቤት ስልጣን በመሆኑ በመጪው መስከረም የመጀመሪያ ሳምንት በሚካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ እንዲፈፀም ወስኗል፡፡” ብሎአል።
የስራ አስፈጻሚው ውሳኔ ለአቶ በረከት ስምኦን ከፍተኛ ሽንፈት መሆኑንና ህወሀት የኦህዴድ የስራ አስፈጻሚ አባላቱን ከጎኑ በማሰለፍ የአቶ በረከትን ቡድን መምታት መጀመሩን ጉዳዩን በቀርበት የሚከታተሉ የኢሳት ምንጮች ገልጠዋል።
የኢህአዴግ ምክር ቤት በመስከረም ወር ሲሰበሰብ ለአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ በመስጠትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትርነቱን ለህወሀት ሰው በመስጠት እስከ 2007 ዓም ይቆያል። ከ2007 በሁዋላ ግን የህወሀት ሊቀመንበር የጠቅላይ ሚኒሰትርነቱን ቦታ እንደሚረከብ ምንጮቻችን ገልጠዋል።
በአቶ በረከት ተንኮል አቶ ሀይለማርያም ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒሰትር እንደሆኑ ተደርጎ ከፍተኛ የቅስቀሳ ስራ የተሰራላቸው በመሆኑ እንዲሁም የአለማቀፉ ማህበረሰብ እና የኢትዮጵያ ህዝብም እርሳቸውን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተቀበላቸው በመሆኑ ይህን ውሳኔ መቀልበስ በኢህአዴግ ውስጥ ክፍፍል እንደተፈጠረና አለመረጋጋት እንዳለ የሚያሳይ በመሆኑ ህወሀት የአቶ ሀይለማርያምን ሹመት በተወሰኑ ማስተካከያዎች ሊቀበለው መዘጋጀቱ ታውቋል።
እነዚህ ማስተካከያዎችም፣ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በአቶ መለስ ጊዜ እንደነበረው ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው ሙሉ አዛዥ የሚሆኑበት አሰራር ተወግዶ፣ እስከመጪው ምርጫ ድረስ፣ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በሚመረጡላቸው ልምድ ያላቸው ሰዎች እየታገዙ እንዲያስተዳደሩ የሚል ነው። ህወሀት አቶ በረከትን ከአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በመነጠል፣ የሞግዚት አስተዳዳር ለመመስረት እየሰራ መሆኑን ምንጫችን ገልጠዋል።
ዜና 2
የፍኖተ ነጻነት ምክትል አዘጋጅ ተደጋጋሚ የግድያ ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው አስታወቁ
የፍኖተ ነጻነት ምክትል ዋና አዘጋጅ የሆኑት አቶ ብዙአየሁ ወንድሙ ለኢሳት እንደገለጡት በተለይ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሁዋላ በተደጋጋሚ ” በቅርብ ቀን ትገደላለህ ” አቶ መለስ ከመቀበሩ በፊት አንተ ትቀበራልህ የሚል የስልክ መልእክት ሲደርሳቸው መቆየቱን አውስተው፣ በዛሬው እለትም ተመሳሳይ መልእክቶች ሲደርሳቸው መዋሉን ተናግረዋል::
“ጉዳዩን ለፖሊስ አመልክተዋል ወይ?” በሚል ከኢሳት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የህግ ባለሙያዎች ተመሳሳይ ምክር ቢሰጡዋቸውም፣ በህግ ተቋሟት ላይ እምነት የሌላቸው በመሆኑ እስካሁን ሳያመለከቱ መቆየታቸውን አቶ ብዙሀአየሁ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድነት ፓርቲ ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ ታግዶ እጁን አጣጥፎ እንደማይቀመጥ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ተናግረዋል።
የአንድነት ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዘካርያስ የማነአብ እንደገለጡት ፓርቲው በልሳኑ ላይ የተጣለበትን እገዳ ለመቃወም ህዝቡ ወደ አደባባይ እንዲወጣ ጥሪ እስከማድረግ የሚደርስ እርምጃ ይወስዳሉ::
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide