በአቶ መለስ መንግስትና በኢትዮጵያ ሙስሊሞች መካከል የተፈጠረው ውጥረት አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል

ሚያዚያ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-የብዙሀኑ ሙስሊም አስተባባሪ ኮሚቴ፤ “በሀሰት ፕሮፓገጋንዳ የመብት ጥያቄዎቻችን አይዳፈኑም”  በሚል ርዕስ ባለ 15 ገጽ መግለጫ በበተነበት በትናንትናው ዕለት፤ መንግስት  በፊናው የማስጠንቀቂያ እና የማስፈራሪያ መግለጫ አውጥቷል።

 የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ባወጣው በዚሁ ረዥም መግለጫ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ   በአብዛኛው የሙስሊም ህብረተሰብ ዘንድ እየተነሳ ያለውን ጥያቄና ተቃውሞ፤ በምርጫ 97 ወቅት ተከስቶ ከነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር አመሳስሎታል።

 “መንግስት  ለእስልምና እምነትና ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ካለው አክብሮት በመነሳት  እያሳዬ ያለው ሰፊ ትዕግስት፤ የተቃውሞው አስተባባሪ የሆነው  ህገ ወጥ ሀይል  ከፍርሀት እየተመለከተው  ነው” ሲልም- የአቶ መለስ መንግስት አለመፍራቱን ጠቅሷል።

 እንደ መንግስት መግለጫ፤ ላለፉት 11 ሳምንታት በ አወሊያ እና በአንዋር መስጊድ  እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ   የብዙሀኑ ሙስሊም ጥያቄ ሳይሆን፤ህግና ስርዓትን አክብረው ለመሄድ ዝግጁነት በሌላቸው ሀይሎች  የሚመራ ነው።

 “ እነዚህ ወገኖች  መንግስትም ሆነ የህዝበ ሙስሊሙ ተቋም የየራሳቸውን ምላሽ እንዳልሰጧቸው በማስመሰል ሰፊ አፍራሽ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እያካሄዱ ከመሆኑም በላይ፤ በ1997 ሀገሪቱን ለብጥበጥ ዳርገው ከፍ ያለ ጉዳት ካደረሱትና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተመደቡ ሀይሎች የጥፋት እንቅስቃሴ ጋር በግላጭ ተመጋጋቢ የሆነ ዘመቻም እያካሄዱ ነው” ሲልም ‘የሀይማኖታችን ይከበር!’ ጥያቄ ባነሱ ሙስሊሞች ላይ ፖለቲካዊ ክስ አሰምቷል።

መግለጫው አያይዞም፦“መንግስት ያሳየውን ትእግስት ከድክመት በመቁጠር ፦” መንግስት ፀረ ህገ መንግሰት ሆኗል-ስለዚህ በህገ መንግስቱ የተጎናፀፍናቸውን መብቶች ሊነጥቀን ተነስቷል በማለት እየተቀሰቀሰ ነው” ብሏል።

 እነዚህ ወገኖች ፖል ቶክና ፌስቡክን የመሳሰሉ ዘመናዊ ሚዲያዎችን ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ በማዋል ግርግርና ሁከት እንዲስፋፋ ከሚሹ በሀገር ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች ከሚተላለፉ የውጭ ሚዲያዎች ጋር በመቀናጀት በሀገሪቱ መንግስት ላይ የሚያካሂዱት የማጥላላት ዘመቻ መረን የለለቀበበት ደረጃ ደርሷል ሲልም- የፌዴራል ጉዳዮች መግለጫ አብራርቷል።

 በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ የተደነገገ ቢሆንም፤ አቶ መለስና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በሀይማኖት ውስጥ ጣልቃ በመግባት የ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች የአህባሽን አስተምህሮ እንዲከተሉ፤ እንዲሁም ባልመረጧቸውና አይወክሉንም ባሏቸው የመጂሊስ አመራሮች እንዲመሩ ግፊት በማድረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

 የተቃውሞው መንስኤም ሆነ እስካሁን ድረስ ህዝበ-ሙስሊሙ በሚያደርጋቸው ተቃውሞዎች እያቀረባቸው ያሉት ጥያቄዎችም በዋነኝነት ከነዚሁ ሁለት ነጥቦች ጋር የተያያዘ ነው- ያልመረጥነው የመጂሊስ አመራር ይነሳልን! መንግስት የአህባሽን አስተምህሮ በግዳጅ ህዝበ-ሙስሊሙ ላይ ለመጫን ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ያቁም!” የሚሉ።

 የህዝበ-ሙስሊሙ ጥያቄዎች  በሀይማኖታዊ መብት መከበር ዙሪያ ላይ ያነጣጠሩ ከመሆናቸውም በላይ እስከዛሬ ድረስ በመስጂዳቸው ተወስነው ባሰሙት ተቃውሞ  በተደጋጋሚ፦”መንግስት ድምፃችንን ይስማ!” እያሉ ሲጠይቁ መደመጣቸው ይታወቃል።

 የአቶ መለስ መንግስት ፤አንድ ጊዜ ከአክራሪዎችና ከአሸባሪዎች፤ ሌላ ጊዜ ከተቃዋሚ ሀይሎችና “ኪራይ ሰብሳቢዎች” ከሚላቸው ወገኖች ጋር እያገናኘ ፖለቲካዊ ምስል እየሰጠው ያለው ፤ይህን “የሀይማኖታዊ መብት ይከበር!” ጥያቄ ነው።

ከዚህም አልፎ በአርሲ-አሰሳ ከተማ በመስጊዳቸው ተወስነው የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ በነበሩ ሙስሊሞች ላይ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተኩስ ከፍተው ሰባት መግደላቸው እና በርካቶችን ማቁሰላቸው ይታወሳል።

 ግድያውን ተከትሎ  ትናንት የፌዴራል ጉዳዮች ያወጣው መግለጫ፤መንግስት መጠነ ሰፊ የሀይል እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን የሚያመለክት ነው።

 የብዙሀኑ ሙስሊም አስተባባሪ ኮሚቴ ደግሞ፦” በሀሰት ክስና ፕሮፓጋንዳ የሙስሊሙን ጥያቄ አዳፍናለሁ ማለት ፈጽሞ የማይታሰብ  መሆኑን ነው ያሰመረበት።

 “ እውነትን እስከያዝን ድረስ፤በሀሰት ተወንጅለን እንታሰራለን ብለን አንፈራም! እንሞታታለን እንጂ ከመብት ጥያቄያችን ወደ ሁዋላ አናፈገፍግም” ነው  እያሉ  ያሉት ብዙሀኑ ሙስሊሞች።

 ለዚህም ይመስላል በ አሰሳ ሰባት ሙስሊሞች  በተገደሉና ሳምንት እና መንግስት  የማስጠንቀቂያ መግለጫ ባወጣ ማግስት  በዋለው በዛሬው የጁምአ ጸሎት እንደ ወትሮው ሁሉ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሙስሊሞች  ጠንካራ የተቃውሞ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ውለዋል።

 ለመንግስት መግለጫ ቀጥተኛ ምላሽ በሚመስል መልኩ በ መቶሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በአንዋር መስኪድ ተገኝተው በአርሲ አሳሳ ከተማ የተገደሉት ሰዎች አሸባሪዎች አለመሆናቸውን እና የመጅሊስ አመራሮችም ከስልጣን ወርደው ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል። ድርጊቱን በስፍራው ተገኝቶ በፊልም የቀረጸው የኢሳት ዘጋቢ እንዳለው በዛሬው እለት የነበረው ተቃውሞ ሙስሊሙ ማህበረሰብ መንግስት ላወጣው መግለጫ ቁብ እንዳልሰጠው የሚያመለክት ነው።

 ይህ በእንዲህ እንዳለ በጎፋ አካባቢ በሚገኘው ጀሙ መስጊድ ሌሊቱን ከፍተኛ የሆነ ተኩስ እንደነበር፣ በአካባቢው የሚገኙ የሙስሊም መሪዎችን ለመያዝ ጥረት መደረጉን ለማወቅ ተችሎአል። በሼክ ኮጀሌ መስጊድ ደግሞ 10 ሰዎች ተይዘው ታስረዋል። አዎልያ ኮሌጅም ዛሬ ተዘግቶ መዋሉን መረጃዎች ደርሰውናል። መረጃዎቹን ከመንግስት በኩል ለማጣራት ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።  

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide