ኢሳት (የካቲት 3 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ መንግስት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰላምና መረጋጋት አምጥቷል ቢልም አሁንም ድረስ በአብዛኛው የሃገሪቱ ክፍሎች ውጥረትና ወከባ መኖሩን ነዋሪዎች ለውጭ መገናኛ ብዙሃን ገለጹ። ሙዚቃ መስማት ወንጀል ሆነ ማሳሰሩንም አስታውቀዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች የከተማዋ የህብረተሰብ ክፍሎች በምሽትና ተሰባስቦ የመወያየትና የመጫወት እንቅስቃሴያቸው አሁንም ድረስ እገዳ ተጥሎበት እንደሚገኝ ለጀርመኑ ዶቼ ዌሌ የእንግሊዝኛ ክፍል አስረድተዋል።
መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላምና መረጋጋት አምጥቷል ሲል በተደጋጋሚ የሚሰጠው መግለጫም የሃሰት ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሰበታ ከተማ ነዋሪዎች ህዝባዊ ተቃውሞ መረጋጋትት ቢያሳይም የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱት የሃይል ዕርምጃ ቀጥሎ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ተግባራዊ ሆኖ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም በወጣቱ ላይ የበቀል ዕርምጃን ለመውሰድ እየዋለ መሆኑን ስማቸውን ማሳወቅ ያልፈለጉ ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ሙዚቃ በማዳመጣቸው ምክንያት ከሶስት ወር በላይ ለእስር ተደርገው የሚገኙ ወጣቶች መኖራቸውን የሚናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ዕስራቱና ወከባው የህብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታን እየጎዳ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሃላፊ የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው ወታደሮችን አሰማርቶ ሰላም ተገኝቷል ማለት አሳማኝ እንዳልሆነ ለዜና አውታሩ ተናግረዋል።
መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ከ20ሺ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ቢገልጽም፣ የኦፌኮ አመራሩ ቁጥሩ ወደ 70 ሺ አካባቢ እንደሚደርስ ይፋ አድርገዋል።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ጭምር በቀንና በሌሊት እየታፈሱ ወደአልታወቁ ስፍራዎች በመወሰድ ላይ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አራተኛ ወሩን ይዞ የሚገኘው የአስቸኳይ ጌዜ አዋጅ ሰላምና መረጋጋት አምጥቷል ሲሉ በቅርቡ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ማስታወቅቸው ይታወሳል።
መንግስት ባለስልጣናት በሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ግን ከስድስት ወር በፊት ይነሳ አይነሳ ማረጋገጫን ሳይሰጡ ቀርተዋል። ይልቁንም እንደሚቀጥል ፍንጭ ሰጥተዋል።