(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 14/2011)በአስተዳደራዊ ችግር እና በሙስና በየፍርድ ቤቱ የሚንገላቱ ካህናትን ታደጓቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባቶች ጥሪ አደረጉ።
ዛሬ በተጀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቅዱስ ሲኖዶሱ ቤተክህነቱን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ በዘረኝነት እንዳይጠቃ ካህናት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በመጪው ክረምት 4 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቤተክርስቲያኒቱ የችግኝ ተከላው ዘመቻ አካል እንድትሆን መጠየቃቸውን ሃራ ዘተዋህዶ የተሰኘ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ድረ ገጽ ዘግቧል።
ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአባቶቹ ባስተላለፉት መልዕክትና ጥሪ መንግስት ቤተክርስቲያኒቱን ያከብራል፣ በሚችለው አቅሙ ድጋፍ ይሰጣል ማለታቸውን ሃራ ዘተዋህዶ የተሰኘ ድረ ገጽ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ባደረጉት ጥሪም ቤተክህነቱን እንዲያጠናከሩ ጠይቀዋል።
ከሙስናና ከዘረኝነት የጸዳ ይሆን ዘንድ አድርጉት ሲሉ የተማጸኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በየቦታው የሰላም አባት ሁኑ ብለዋል።
ከቀትር በኋላ በተደረገው የሲኖዶሱ የርክበ ካህናት ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአስተዳደራዊ ችግርና በሙስና በየፍርድ ቤቱ የሚንገላቱትን ካህናት በተመለከተም ለስብሰባው ተሳታፊ አባቶች መልዕክት አስተላልፈዋል።
እነዚህን ካህናት መታደግ አለባችሁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ችግርን የሚያወራ እንጂ ችግርን የሚፈታ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር በቅርበት ለመስራት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
በሰላምና በልማት ጉዳዮች ከእናንተ ጋር ለመስራት የመንግስትን ዝግጁነት አረጋግጥላችኋለሁ ብለዋል።
የኢሳት የቤተክህነት ምንጮች እንደሚሉት ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ዘረኝነትና ሙስና አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱ በስፋት እየተነሳ ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውጭና ሀገር ውስጥ ባሉ አባቶች መካከል እርቅ ከተፈጠረ በኋላ ወደ አንድነት ለመምጣት የሚደረገው ሂደት የተለያዩ እንቅፋቶች እንደገጠሙት ይነገራል።
በተለይም ዘረኝነት አንዱ ችግር ሆኖ እንደሚጠቀስ ነው የመረጃ ምንጮች የሚገልጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአንድነት ጉባዔ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በዘረኝነት ከወደቀ ክርስቶስን ረሳን ማለት ነው ሲሉ ለአባቶቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ህዝቡን አስተዋውቁ፣ አዋህዱ፣ የሰላም መሪዎች እንድትሆኑ እንሻለንም ብለዋል።
በሌላ በኩልም በመጪው ክረምት ላይ በመንግስት በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ቤተክርስቲያኒቱ ሚናዋን እንድትወጣ ጥሪ አድርገዋል።
ቤተክርስቲያን ዛፎችን መትከል ብቻ ሳይሆን መጠበቅም ታውቅበታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በክረምት ለሚደረገው የ4ሚሊዮን ችግኞች ተከላ ቤተክርስቲያኒቱ እንድታግዘን ጥሪ እናደርጋለን ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከ25 ዓመታት በላይ ተለያይተው የነበሩትንና በሁለት ሲኖዶስ ስር የቆዩትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አባቶችን በማስታረቅ በአንድ ሲኖዶስ ስር እንዲሆኑ ለተጫወቱት ሚና ቤተክርስቲያኒቱ ምስጋና ማቅረቧም ተመልክቷል።