በአሰላ ከተማ የኮማንድ ፖስት አባላት ነን ያሉ ሰዎች እናትና ልጅ ገደሉ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 11 ቀን 2010 ዓ/ም) ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአሰላ ከተማ የኮማንድ ፖስት አባላት አንድ የ15 አመት ልጅ እና እናቱን መግደላቸውን እንዲሁም 4 ሴቶችን ማቁሰላቸውን የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
ወታደሮቹ በቀበሌ 10 ውስጥ ነዋሪ የሆኑትን የአቶ አህመድ በሽሬን ቤት ሰብረው በመግባት የ15 አመቱን እስማኤል አህመድን እና እናቱን ወ/ሮ ዘይነባ አሊን ሲገድሉ ሌሎች 4 ሴት ልጆቹን ደግሞ አቁስለዋል። የቤቱ አባ ወራ ደግሞ በወታደሮች ታፍነው ተወስደዋል።
ወታደሮቹ እርምጃውን የወሰዱት አቶ አህመድ የኦነግ አባል ነው በሚል ምክንያት ነው።
አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ከተሾሙ በሁዋላ ወታደሮች በቡሌ ሆራና ሞያሌ ከተሞች በዜጎች ላይ የመግደል እርምጃዎችን ወስደዋል። በሞያሌ የሶማሊ ልዩ ሃይል ባፈነዱት ቦንብ 4 ሰዎች ሲገደሉ ከ60 በላይ ደግሞ ቆስለው ነበር። ዛሬ በአሰላ የተፈጸመው ግድያ ዶ/ር አብይ አህመድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስነሳት እንዲሁም የኮማንድ ፖስት አባላት የሚፈጽሙትን ግድያ የማስቆም ፍላጎት ወይም አቅም የላቸውም በሚል የሚቀርብባቸውን ትችት የሚያጠናክር ነው። የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ሊግ ባወጣው መግለጫ፣ ዶ/ር አብይ ከተሾሙ በሁዋላ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ግድያ ጨምሯል ብሏል።
በግድያው ዙሪያ የኦሮምያ ክልል አስተዳደር የሰጠው መግለጫ የለም።