(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 2/2011)በደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ ቡኒቲ ቀበሌ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች አካባቢውን ለቀው እንዲፈናቀሉ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ ።
ነዋሪዎቹ ለኢሳት እንደገለጹት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የተደረገው በቀበሌ አመራሮች ውሳኔ ነው።
ባለፈው መስከረም ጀምሮ ሶስት ጊዜ ከአካባቢው እንድንፈናቀል ተደርገናል የሚሉት ነዋሪዎቹ አሁንም ጉማይዴ ተብሎ በሚጠራው አካባቢው መስፈራቸውን ነው የሚናገሩት።
ኢሳት ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ደቡብ ክልል ስልክ ቢደውልም ሊሳካለት አልቻለም።
የአማራ ክልል ምክትል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሕሊና መብራቱ ግን ስለጉዳዩ መረጃ አለን ሲሉ ለኢሳት ቢገልጹም ሙሉ መረጃውን ለመስጠት ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም።
ባለፈው አመት ጷጉሜ 2010 ነው የቀበሌው አስተዳዳሪ አቶ ባይናክ በዙና ምክትላቸው ሕጻናት ከአዋቂ ሳይለዩ የአማራ ተወላጆችን ስብሰባ ጠሩን ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት።
በስብሰባውም ግልጽ ባለ መልኩ ይሄ የእናንተ መኖሪያ አይደለምና ወደ መጣችሁበት ተመለሱ ተባልን ይላሉ።የእናንተ መኖሪያ ክልል 3 ስለሆነ ወደዛ ሂዱ የሚል መመሪያ መተላለፉን በመግለጽ
ተወላጆቹ እንደሚሉት በዚህ አካባቢ ከሃምሳ አመት በላይ ነው የኖርንው።ዛሬ ላይ ተነስቶ መኖሪያህ አይደለም ማለት ግን እጅግ የሚያሳዝንና ሃገራችን ወዴት እየሄደች እንደሆነ የሚያመላክት ነው።
ከአካባቢው መልቀቅ ብቻ ሳይሆን እስርና ድብደባው ተበራክቷል በአካባቢው ያለው ሃይልም ሊከላከልልን አልቻለም ብለዋል።–በስፍራው የነበረው የመከላከያ ሃይል አይመለከተኝም ማለቱን በመግለጽ
ከአካባቢው ማፈናቀል ብቻ ሳይሆን ከብቶቻቸውና አጠቃላይ ለፍተው ያፈሩትን ንብረት መዝረፍም ዋነኛ ተጋብራቸው ሆኗል ያላሉ ተፈናቃዮቹ።
ከአካባቢው የተፈናቀሉትና ወደ ጉማይዴና ቅርብ ወደ ሆኑ አካባቢዎች የሄዱት የአማራ ክልል ተፈናቃዮች ቁጥርም ቢሆን ከ2 ሺ በላይ ነው ብለዋል ተፈናቃዮቹ
ባለፈው መስከረም ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ጊዜ ተፈናቅለን ወደ አካባቢው እንድንመለስ ቢደረግም።አሁን ግን ለሶስተኛ ጊዜ አካባቢውን ለቀን እንድንወጣ ተደርገናል ብለዋል።
እየደረሰብን ያለን ችግር በተደጋጋሚ ለክልሉ ብናሳውቅም ጆሮ የሚሰጥን አላገኘንም ብለዋል።
ለአማራ ክልል አቤት ብለን ከክልሉ አመራሮች መተው የአማሮ ወረዳ አመራሮችን ለመነጋገርና ጉዳዩን ለማረጋጋት ቢሞክሩም የአማሮ አመራሮች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊሳካ አልቻለም ብለዋል።
ኢሳትም ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ደቡብ ክልል ስልክ ቢደውልም ሊሳካለት አልቻለም
የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ሕሊና መብራቱ ስለጉዳዩ መረጃ አለን ቢሉም ለኢሳት ግን መረጃውን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።