የጅማ ህክምና ማዕከል የጤና ሰራተኞች የስራ ማቆም አደረጉ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 2/2011)በጅማ ዩኒቨርሲቲ የጅማ ህክምና ማዕከል የጤና ሰራተኞች የስራ ማቆም አደረጉ።

ሰራተኞቹ የስራ ማቆም አድማውን የመቱት ባለፈው እሁድ ሌሊት በማዕከሉ ድንገተኛ ክፍል ባልታወቁ ሃይሎች ሁለት በልምምድ ላይ ያሉ ዶክተሮችን የግድያ ሙከራና በሌሎች ባለሙያዎች ላይ ደግሞ ጉዳት ማድረሳቸውን ተከትሎ ነው።

ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ምንም ዓይነት የመከላከል ርምጃ አለመወሰዱን የጠቀሱት ሰራተኞቹ ለህይወታቸው ዋስትና ባለመኖሩ ስራቸውን ለማቆም መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ሰላምን ማስቀደም ጤናን ማስቀደም ነው በሚል ለኢሳት የደረሰው የጅማ የጤና ማዕከል ሰራተኞች አቤቱታ ላይ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ተጠይቋል።

በጉዳዩ ላይ የጅማ ዩኒቨርስቲን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።