በአማራ ክልል ጭልጋ ወረዳ ግጭት ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 30/2011)በአማራ ክልል ጭልጋ ወረዳ ባለፉት ሁለት ቀናት ግጭት መቀስቀሱ ተሰማ።

ከአይከል እስከጓንግ ባለው መስመር ሁለት ቀበሌዎች መውደማቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ለኢሳት እንደገለጹት ሰሞኑን ባገረሸ ጥቃት በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ ሰዎች ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተሰደዋል።

አፈናና ዝርፊያም በስፋት እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት እየሰራ ቢሆንም በውክልና የሚደረግ ግጭት በመሆኑ በቶሎ ለመፍታት አልቻልንም ብለዋል ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ።

ግጭቱ የተባባሰው ህወሃት በእጅ አዙር የሚያካሂደው፣ በመሳሪያና በገንዘብ የሚደግፈው ግጭት በመሆኑ ነው ሲሉም ገልጸዋል።