ሎረን ባግቦ ከወህኒ ወጡ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 29/2011)በአለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተከሰው በወህኒ የቆዩት የአይቮሪኮስቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሎረን ባግቦ ከወህኒ መውጣታቸው ተሰማ።

ሎረን ባግቦ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላም ወደ ቤልጂየም መጓዛቸው ታውቋል።

በቁም እስረኝነት በቤልጂየም እንዲቆዩ ከኔዘርላንድ ሔግ ወህኒ ቤት ዛሬ የተለቀቁት ሎረን ባግቦ ፓስፖርታቸውንም እንዲያስረክቡ ቅድመ ሁኔታ ተጥሎባቸዋል።

የአይቮሪኮስት መሪ በነበሩበት ወቅት ፈጸሙት በተባለው ወንጀል ጉዳያቸው በአለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዘሔግ ኔዘርላንድ ሲታይ ቆይቷል።

አቃቤ ሕግ በቂ መረጃ አላቀረበም በሚል የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የቀድሞውን የአይቬሪኮስት መሪ እንዲለቀቁ ወስኗል።

ሆኖም በወህኒ ውስጥ ለተጨማሪ አንድ ወር ከቆዩ በኋላ በቅድመ ሁኔታ ተፈተው አርብ ዕለት ቤልጂየም መግባታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

ባልታወቀ ቦታ ቤልጂየም ውስጥ መቀመጣቸው የተገለጸው ሎረን ባግቦ በቁም እስር ላይ ሲሆኑ ፓስፖርታቸውንም አስረክበዋል።

ቤልጂየም ለ90 ቀናት በሐገሯ እንዲቆዩ ቪዛ የሰጠቻቸው ሲሆን አቃቤ ህግ መረጃውን አሟልቶ ክሱን እንደገና ሲያንቀሳቅስ ሎረን ባግቦ ወደ ሔግ ኔዘርላንድ ወህኒ ቤት እንደሚዛወሩም ተመልክቷል።

ከ8 አመታት በፊት በአይቬሪኮስት በተካሄደ ምርጫ በተቃዋሚው መሪ ዶክተር ኦላሳን ዋተራ በመሸነፋቸው ስልጣን አለቅም ያሉት ዶክተር ሎረን ባግቦ በተነሳባቸው አመጽ ከቤተመንግስት የውስጥ ሱሪ እንደለበሱ ተጎትተው ወደ ወህኒ ቤት መወሰዳቸው ይታወሳል።