(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 25/ 2011) በአማራ ክልል በፖሊስ ላይ የቅጣት ውሳኔ በመስጠታቸው የታሰሩት ዳኛ ጉዳይ ዳኞችን ሥጋት ውስጥ መክተቱ ተነገረ።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሞጣ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ አንድ የፖሊስ አባል በአንድ ወር እስራት እንዲቀጣ በሰጡት ውሳኔ ምክንያት መታሰራቸው፣ ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ዳኞችን ሥጋት ውስጥ መጣሉ ተገልጿል።
የታሰሩት ዳኛ አቶ ምሥጋናው ባቡር ይባላሉ። አቶ ምስጋናው የሞጣ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ ናቸው፡፡ በችሎት ተሰይመው እያለ በምስክርነት የተቆጠሩ ግለሰቦች በፖሊስ መደብደባቸውን ሲነግሯቸው እውነትነቱን ካጣሩ በኋላ አጃቢ ፖሊሱን በእስራት እንዲቀጣ ውሳኔ መስጠታቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ የኔነህ ስመኝ ገልጸዋል፡፡
የፖሊስ ኮሚሽኑ የወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም ለቀጣይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱ ይነገራል።
ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የወረዳው ዳኛ በፖሊሱ ላይ ዕርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት በምርመራ እንዲጣራ ትዕዛዝ መስጠት ሲገባቸው ያንን ሳያደርጉ የሰጡት ውሳኔ ተገቢ እንዳልሆነ መግለጹም ነው የተነገረው።
እናም ሥልጣናቸውን ያላግባብ ተጠቅመዋል በሚልም የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ውድቅ እንዳደረገው አቶ የኔነህ ገልጸዋል፡፡
ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም መሆኑን ሲያሳውቅም ይሕን የሰማው የወረዳው ፖሊስ፣ ለዞኑ ፖሊስ መምርያ በመንገርና ትዕዛዝ በመቀበል ዳኛውን በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ የኔነህ ስመኝ ይሕኝን ጉዳይ እንደሰሙ ለወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ትዕዛዝ በመስጠታቸው ዳኛው ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ከእስር መፈታታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡
አንድ ዳኛ በያዘው መዝገብ ላይ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ቢሰጥ እንኳን፣ በይግባኝ ውሳኔውን ከማሻርና ከዚያም ካለፈ በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በኩል ከማስጠየቅ በስተቀር መታሰር እንደሌለበት ሕጉ ይደነግጋል፡፡ የተደረገውና የተወሰደው ዕርምጃ የሚወገዝና ፍፁም ስህተት መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ዳኞች ያለመከሰስ መብት እንዴት እንደ ሌላቸው ተጠይቀው፣ ቀደም ብሎ ለክልሉ ምክር ቤት ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም በወቅቱ የነበረው የምክር ቤት እንኳን በአዋጅ ሊያፀድቀው ቀርቶ፣ ለውይይት እንኳን እንዳላበቃው አስታውቀዋል፡፡ አሁንም ለምክር ቤት አቅርበው ለማፀደቅ እየሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአቶ ምሥጋናውን መታሰር የሰሙ አንዳንድ የክልሉ ዳኞች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከፍተኛ ድንጋጤ ተሰምቷቸዋል፡፡ ይኼን ሕገወጥ አካሄድ የሰማ ፖሊስም ሆነ ሌላ አካል ከዚህ በኋላ የሕግ የበላይነትን አክብሮ ለሕግ ተገዥ ስለመሆኑም ጥርጣሬ እንዳደረባቸውም ገልጸዋል፡፡
ለማንኛውም ዜጋ የሕግ የበላይነት መተኪያ የሌለው መሆኑን፣ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩበት እንደሚገባም ጠይቀዋል።