ሰኔ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል በስምንት ዞኖች ከፍተኛ የሆነ የተምች ወረርሺኝ በመከሰቱ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡
ችግሩን ለመከላከል እስካሁንም አጥጋቢ እርምጃ አለመወሰዱን አርሶ አደሮች ይናገራሉ።
ክልልሉ የግብርና ቢሮ የኤክስቴንሺን የስራ ሂደት ሃላፊ አቶ ላንተይደሩ ተስፋየ እንደተናገሩት በክልሉ በሚገኙ በ64 ወረዳዎች በ434 ቀበሌዎች የተከሰተው የተምች ወረርሺኝ በ62 ሺ 87 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት አድርሷል።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከ36 ሺ ሄክታር ያላነሰ መሬት በበቆሎ ፤በማሺላ ፤በቦሎቄ ፤በገብስና በዳጉሳ የተሸፈነ ነው፡፡
እንደ አቶ ላንተይደሩ ተስፋዩ ገለጻ በምዕራብ ጎጃም እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በሰብል የተሸፈነው መሬት ላይ የተከሰተውን የተምች ወረርሺኝ በመድሀኒት እና በባህላዊ ዘዴዎች ለመከላከል ሙከራ ተደርጎአል። ባለስልጣኑ እንዳሉት በአንጻራዊ መልኩ የቀነሰው የተምች ወረርሽኝ በሚቀጥሉት ወራት ተመልሶ ከመጣ በምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልዋል። የፌደራል መንግስት 40 ሺ ሊትር መድሀኒት እንዲልክላቸው ጠይቀው 7 ሺ እንደገባላቸው ባለስልጣኑ አክለው ተናግረዋል::