በአማራ ክልል የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደሌሎች አካባቢዎችም እየተስፋፋ ነው

ኢሳት (ነሃሴ 23 ፥ 2008)

በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በተያዘው ሳምንት ወደ አዳዲስ አካባቢዎች መዛመቱን ተከትሎ፣ የአገዛዙ ሃላፊዎች በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ እንደገቡና ህዝባዊ ተቃውሞንም በሃይል ለመጨፍለቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየመከሩ እንደሆነ ተነገረ። ህዝባዊ ተቃውሞ በተለይም በሰሜን በጎንደር፣ ደባርቅ፣ ዳባት፣ ገብደብየ፣ አምባጊወርጊስ፣ ጎንደር፣ ደምቢያ፣ አዲስ ዘመን፣ በለሳ፣ ወረታ፣ ዓለም በር፣ ደብረ ታቦር፣ ጋሳይ- ክምር ድንጋይ፣ ነፋስ መውጫ፣ ሳሊ፣ ጨጭሆ፣ ጎብጎብ፣ ፍላቂት፣ ደራ ሐሙሲት፣ አድማሱን በማስፋት በሌሎች በትናንሽ ከተሞች ጭምር በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ ታውቋል።

ህዝባዊ እምቢተኝነቱ በምዕራብ ጎጃም፣ አዊና፣ ምስራቅ ጎጃም ከተሞች፣ ባሕር ዳር፣ ፒኮሎ፣ ዱርቤቴ፣ አቸፈር፣ ቋሪት፣ ዳንግላ፣ እንጅባራ (ኮሶበር)፣ ቲሊሊ፣ ቡሬ፣  ፍኖተ ሰላም፣ ብርሸለቆ፣ ጃቢ ጠህናን፣ ሽንዲ፣ ደምበጫ፣ የጨረቃ፣ አንበር፣ ሎማሜ፣ ፈረስ ቤት፣ አዴት፣ ይልማና ዴንሳ፣ ጎንጅ ቆለላ፣ ሞጣ፣ ጉንደወይን ተስፋፍቶ የምዕራብና የምስራቅ ጎጃም አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ከመንግስት አገዛዝ ቁጥጥር ውጭ ማድረጉ ታውቋል።

የክልሉ ባለስልጣናትና የህወሃት አመራሮች ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣቱ በፊት በሃይል ለመቀልበስ እየተመካከሩ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል። የህወሃት ኢህአዴግ ባለስልጣናት በቀጣይ የሚወስዱት እርምጃ ምን መሆን አንዳለበት እየመከሩ እንደሚገኙ የሚናገሩት የኢሳት ምንጮች፣ ተቃውሞው ወደ ወሎና ሰሜን ሸዋ እንዳይስፋፋ ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

ህዝባዊ ተቃውሞው በሰላማዊ ሰልፍ ብቻ ሳይገደብ በቤት ውስጥ አድማም ተጀምሯል። በጎንደር ወረታ ፣ ጋይንት ፣ ደብረታቦር እስቴ የቤት ውስጥ ኣድማውን መቀጠላቸው ታውቋል። በጎንደር ከተማ የስራ ማቆም አድማው ላለፉት 6 ቀናት እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት የኢሳት ምንጮች፣ በፍኖተ ሰላምም የቤት ውስጥ አድማው ተጠናክሮ መቀጠሉ ተነግሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በብር ሸለቆ የአርሷደር ታጣቂዎች ከወታደሩ ጋር ግጭት ተፈጥሮ ቁጥራቸው ያልታወቁ የመንግስት ወታደሮች እና ታጣቂ ገበሬዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ለኢሳት መረጃ ያደረሱ እማኞች ከስፍራው ዘግበዋል።