(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 26/2010)በአማራ ክልል ታስረው የነበሩ 19 ጋዜጠኞችና ምሁራን መለቀቃችውን ዘገባዎች አመለከቱ።
በእስር ላይ የቆዩት አስራ ዘጠኙ ምሁራን እና ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ በአማራ ክልል ዘመቻ ተጀምሮ ነበር።
ከባህርዳር ከተማ አስቸኳይ አዋጁን ጥሳችኋል ተብለው በእስር ላይ የቆዩት እነዚሁ ምሁራንና ጋዜጠኞች ሁሉም ተለቀዋል።
በድጋሚ የታሰሩት እነ እስክንድር ነጋ ግን አሁንም ከእስር አለመለቀቃቸው ታወቋል።
በአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም ተንቀሳቅሳችኋል በሚል ከመጋቢት 15/2010 ጀምሮ በእስር ላይ የነበሩት ምሁራንና ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ የለውጥ አራማጆች ዘመቻ ጀምረው ነበር።
እስረኞቹ ካልተለቀቁ በአማራ ክልል አድማ ለመጀመር ወረቀቶች ሲበተኑና ማስጠንቀቂያ ሲሰጥም ቆይቷል።
ይህንኑ ተከትሎም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችኋል በሚል የታሰሩት 19ኙ ምሁራንና ጋዜጠኞች በሙሉ ተለቀዋል።
ከተለቀቁትም መካከል ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ መምህር፣ተመስገን ለማ የወሎ ዩኒቨርስቲ መምህር፣በለጠ ማሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር፣ካሱ ሃይሉ የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ መምህር፣አዲሱ መለሰ የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ መምህርና የሱፍ ኢብራሒም የተባሉ ጠበቃም ይገኙበታል።
ከእስር ከተለቀቁት ከነዚሁ እስረኞች መካከልም የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ንጋቱ አስረስ እና በለጠ ካሳ የተባለ ጋዜጠኛም ከእስር ተለቀዋል።
ቀሪዎቹ ተፈቺዎችም የሕዝብ ተቆርቋሪነት ስላላቸው ብቻ ታስረው የነበሩ ናቸው ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በድጋሚ የታሰሩት እነ እስክንድር ነጋ ዋስትና ቢፈቀድላቸውም አሁንም አለመፈታታቸው ነው የተነገረው።
እስክንድር ነጋን ጨምሮ እስር ቤት የታጎሩት 12 ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ምንም ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ቤት እንደሚገኙ ታውቋል።
በተደጋጋሚ እንደሚፈቱ ከተገለጸ በኋላ ዛሬም በማጎሪያ ቤት የሚገኙት የዋልድባ መነኮሳት አሁንም በእስር እየማቀቁ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል።
የግንቦት 7 መስራች የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌንና የኢትዮጵያ አየር ሃይል አብራሪዎች የነበሩት እነ የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችም አሁንም በወህኒ እንደሚገኙ ይታወቃል።