ነሃሴ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል የተጀመረው ተቃውሞ እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት የአጋዚ ወታደሮች በህዝቡ ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል። ትናንት በሰሜን ጎንደር የመተማ ከተማ በተካሄደው ተቃውሞ ፣ ድንበር ጠባቂዎችና አካባቢ ሚሊሺዎች በህዝብ ላይ ለመተኮስ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ፣ የአጋዚ ወታደሮች ወደ ስፍራው ደርሰው ከ20 ያላነሱ ሰዎችን ሙትና ቁስለኛ አድርገዋል። ወታደሮቹ በህዝብ ላይ በቀጥታ መተኮሳቸውን ተከትሎ ህዝቡ በቁጣ ጎማዎችንና ሌሎች የገዢው ፓርቲ ምልክት የሆኑ ነገሮችን ሁሉ አቃጥሏል። በአምባጊዮርጊስ ተቃውሞው ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል። የአጋዚ ወታደሮች ከአካባቢ ሚሊሺያዎች ጋር በመሆን በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ፈጽመዋል።
በጋይንት ደግሞ በርካታ የአጋዚ ወታደሮች የተሰበረውን ድልድይ ለመጠገን በብዛት ወደ ከተማው መግባታቸውን ተከትሎ ነዋሪዎች ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።
በባህርዳር አሁንም ህዝቡ ከቤት ያልወጣ ሲሆን፣ ወታደሮች ወጣቶችን ከቤታቸው እያወጡ ወደ እስር ቤት መውሰዳቸው ታውቛል።
ማምሻውን በደረሰን ዜና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጊቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል፡፡
በደብረማርቆስም የስራ ማቆም አድማው ሲቀጥል በደብረታቦር ደግሞ ከስራ ማቆም አድማው በሁዋላ ነዋሪዎች ስራ ሲጀምሩ ሾፌሮችና ነጋዴዎች ታስረዋል። በርካታ የንግድ ቤቶችም ታሽገዋል። የደብረታቦር እስር ቤት ከውስጥ በተነሳ እሳት ቃጠሎ የደረሰበት ሲሆን፣ በርካታ እስረኞች አጋጣሚውን በመጠቀም አምልጠዋል። ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል። ምን ያክል እስረኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡ የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን በማቋረጥ ወደ የመጡበት አካባቢ ተመልሰዋል።
በምዕራብ ጎጃም አዊ ዞንም እንዲሁ በርካታ ወጣቶች ከቤታቸው እየታፈሱ ታስረዋል።
በደሴ ከ3 ሺ 500 በላይ የብአዴን አባላት ስብሰባ ረግጠው ወጥተዋል። 8 ሰአት ከ20 ደቂቃ ላይ ወደ 5 ሺ የሚደርሱ የደሴ ከተማ የብአዴን አባላት በመምህራን ትምህርት ኮሌጅ በእንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው እና በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ወ/ሮ ገነት ዘውዴ እየተመሩ ስብሰባውን ያካሄዱ ሲሆን፣ ሚኒስትሩ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ መንግስትን ለማፍረስ የቀረበ የትምክተኞች ሴራ እንጅ የህዝብ ጥያቄ አይደለም ብለው በመናገራቸው የብአዴን አባላቱ በከፍተኛ ድምጽ ተቃውሞአቸውን ግለጸዋል። ሚኒስትሩ ተቃውሞው መንግስትን ለመገልበጥ ትምክተኞች የጠነሰሱት ሴራ በመሆኑ ሁላችሁ ራሳችሁን ብትከላከሉ ጥሩ ነው፣ ያ ካልሆነ ግን ህዝብ ፊት እየቀረብክ ትበጠራለህ ሲሉ አክለዋል። ተሰብሳቢዎች በድርጅታቸው ላይ ተስፋ እየቆረጡ መምጣታቸውን በመናገር 9 ሰአት ከ55 ደቂቃ ላይ ከ 3 ሺ 500 በላይ አባላቱ ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የብአዴን አባላት ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸው፣ የድርጅቱ አብዛኛው አባላት ከህዝብ ጎን መቆማቸውን ያሳዩበት ነው ሲሉ ለኢሳት ገልጸዋል።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ም/ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ መልኬ ታደሰ የቢሮ ሰራተኞችን ሥራ እንዲገቡ በማዘዝ ካልገቡ ግን ኢህአዴግ እንደተሸነፈ ይቆጠራል በማለትና ደመወዝ እንደሚቆረጥባቸው ለማስፈራራት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።