መስከረም ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከ8 ሺ 800 በላይ ሰዎች በመልሶ ማልማት የተነሳ እንደሚፈናቀሉ ከክልሉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ተፈናቃዮች እንደሚሆኑ ያወቁ ነዋሪዎች በከፍተኛ የኑሮ ችግር ውስጥ ወድቀናል ሲሉ አማረዋል።በአማራ ክልል በሚገኙ በሶስቱ የክልሉ ሜትሮፖሊታን ከተሞች ማለትም በባህርዳር፣ደሴና ጎንደር በመልሶ ልማት የሚፈናቀሉ 5 ሳይቶች ተለይተው ተከልለዋል፡፡ በባህርዳር በመጀመሪያው ዙር 431 የቀበሌ ቤት ተከራዮች ፣ 2 ሺ 155 ቤት ተጋሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ፣ 77 የግል ባለይዞታዎች ባጠቃላይ 2 ሺ 540 የከተማዋ ነዋሪዎች ከሚኖሩበት የይዞታ እና የኪራይ ቤት እንደሚፈናቀሉ ከክልሉ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ የደረሰን መረጃ አመልክቱዋል፡፡ ለተፈናቃዩች እንደምርጫቸው በኮንደሚኒየምና በአነስተኛ ወጭ በሚገነቡ ቤቶች እንዲስተናገዱ ለማድረግ ከክልሉ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ጋር በጋራ ለመስራት እንቅስቃሴ ቢደረግም ስኬታማ ሳይሆን መቅረቱም ታውቋል፡፡ በጎንደር ከተማም በመልሶ ልማት ሳይት ውስጥ ከይዞታቸው የሚፈናቀሉ 661 የመንግስት ቤት ተከራዮችና 472 የግል ባለይዞታዎች በጥቀሉ ከ5 ሺ 660 በላይ ነዋሪዎች ይፈናቀላሉ፡፡
በደቡብ ወሎ ደቡብ ጎንደር፣ሰሜን ወሎ እና አዊ ዞን ከተሞች 5 ሚልዮን 242 ሺ 569 ሄክታር የአርሶ አደር መሬት በኢንቨስትመንት ስም ለተለያዩ ተግባሮች ቢሰጥም ልማት ሊከናወንባቸው ባለመቻሉ፣ የአርሶአደሩ መሬት ለአመታት ጾም እንዲያድር መደረጉን ተያይዞ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የክልሉን ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።