ህዳር 26 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ስማቸውን መግለጥ ያልፈለጉ የክልሉ መምህራን እንደሚሉት፣ መንግስት የክልሉን የመምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት፣ አቶ መንግስቱ አህመዴን፣ ከስልጣን ለማስወገድ የጀመረውን ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠሉ ፣ በመምህራን እና በመንግስት መካከል ያለው ፍጥጫ እንዲጨምር አድርጎታል።
የመንግስት ባለስልጣናት በተለያዩ የወረዳ ትምህርት ቤቶች ተገኝተው “የማህበሩ ሊቀመንበር የግንቦት7 አባል ነው፤ መምህራን የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያደርጉ እና ከመንግስት ጋር እንዲጋጩ እየቀሰቀሰ ነው” በማለት መናገራቸው ታውቋል።
መምህራን በበኩላቸው ” የማህበሩ ሊቀመንበር ከስልጣን የሚወገድ ከሆነ፣ መምህራን የራሳቸውን እርምጃ ይወስዳሉ” በማለት እያስጠነቀቁ ናቸው። በመምህራን የአቋም ጽናት የተደናገጠው መንግስት ፣ ፕሬዚዳንቱ ከአገር አቀፉ መምህራን ማህበርም ሆነ ከሌሎች ንኡስ ማህበራት ጋር እንዳይገናኝ አድርጓል።
መምህር መንግስቱ ናዝሬት ተካሂዶ በነበረው አለማቀፍ የመምህራን ጉባኤ ላይ “የመምህራንን የደሞዝ ጭማሪ፣ የደረጃ እድገትንና የማስተማርና ሀሳብን የመግለጽ መብቶች ፣ ከሁሉም በላይ መምህራን ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ እንዲሆኑ፣ በሰለማዊ ሰልፍ ሳይቀር መብታቸውን እንዲጠይቁ ሊፈቀድላቸው ይገባል” የሚሉ ሀሳቦችን ከሰነዘሩ በሁዋላ ሀሳባቸውም ለውይይት አለመቅረቡ ስላበሳጫቸው ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው መዘገቡ ይታወሳል።
መምህር መንግስቱ በክልሉ መምህራን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያላቸው እንደሆኑ ይነገራል። ፕሬዚዳንቱ “አድማ እንዲያደርጉ እያበረታቱ ነው፣ የግንቦት7 ህቡእ አባል ናቸው” በሚሉ ተልካሻ ሰበቦች ለእስር ሳይዳረጉ እንደማይቀርም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የመለስ መንግስት አንጋፋውን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርን ካፈረሰ በሁዋላ፣ ለመምህራን መብት የሚቆረቆር ጠንካራ ድርጅት እንዳይወጣ ማድረጉ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።