ግንቦት ፬ ( አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልል የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ እውነቴ አለነ ፤ ግለሰቦቹ የተቀጡት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገ ጠንካራ የክትትልናየቁጥጥር ስራ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ነው በማለት ለመንግስት መገናኛ ብዙሀን ገልጸዋል።
ከተከሳሾቹ መካከል 182ቱ ወንድና 29ኙ ሴቶች ሲሆኑ፤በተመሰረተባቸው በስልጣን ያለ አግባብ በመጠቀም፣ በግዢና ጨረታ ሙስና፣ በተጭበረበረ ሰነድበመገልገል፣ በግብር መሰወርና በመሰል የወንጀል ክሶች ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል ሲሉ ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸውም ከሦስት ወር አስከ 14 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ300እስከ 30 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው አቶ እውነቴ ገልጸዋል።ከፍተኛ ባለሥልጣንን የሚፈራውና በቅጽል ስሙ “ጥርስ የሌለው አንበሳ” ተብሎ የሚጠራው የጸረ ሙስና ኮሚሽን፤ የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ይታወቃል።
ገዥው ፓርቲ ተቃውሞ ባየለበት ጊዜ የሙስና ካርዶችን በመምዘዝ ብዙዎችን ዘብጥያ የመወርወር ልምድ ከማካበቱ አኳያ አሁን ከኃላፊነታቸው የተነሱትና ቅጣት የተጣለባቸው ሠራተኞች በሙሉ ሙስና ፈጽመው ነው ብለው ለማመን እንደሚቸገሩ ታዛቢዎች ተናግረዋል።
በተለይ ባለፈው ዓመት ሕዝባዊ ተቃውሞ በተቀጣጠለባቸው በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በርካቶች በጅምላ በሙስና ክስ ከኃላፊነታቸው እየተወገዱና እየታሰሩ ይገኛሉ።