የካቲት 7 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአንድነት ሊቀመንበር ዶክተር ነጋሶ ይህን ያሉት፤ ሰሞኑን የካቲት 3 ቀን ምሽት በፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት እነ አንዷለም አራጌን ለማስታወስ በተካሄደው የሻማ ማብራት ዝግጅት ላይ ነው።
“እነ አንዷለም ከታሰሩ ስድስት ወር ሆናቸው….” በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ዶክተር ነጋሶ፤ በእርሳቸው እምነት አንዱዓለምም ሆነ ናትናኤል ንጹህ ሰዎች መሆናቸውን፤እንዲሁም የኦፌዴን ም/ ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባና የኦህኮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኦልባና ሌሊሳ የታሰሩትም፤ የሽብር ተግባር ስለፈጸሙ ሳይሆን የአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ተወካዮችን በማነጋገራቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
“በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ 130 የህሊና እስረኞች አሉ”ያሉት ዶክተር ነጋሶ፤ ከእነዚህ የህሊና እስረኞች መካከል የአንድነት ፓርቲ ም/ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዱዓለም አራጌና የፓርቲያችን ብ/ም/ቤት አባል ናትናኤል መኮንን ይገኙበታል ብለዋል።
“ግንቦት 7 ለማንኛውም ሰው ‘እንኳን አደረሳችሁ!’ እያለ የሚልከው መልዕክት በአንዱዓለም ኢሜልም መላኩን፤ ነገር ግን አንዱዓለም ለግንቦት ሰባት የሰጠው መልስ አለመኖሩን ተረድቼአለሁ” ያሉት የአንድነቱ ሊቀ-መንበር፤ ይህ ነገር በአንዷለም ክስ ላይ እንደማስረጃ መቅረቡ እንዳስገረማቸው ጠቁመዋል።
ሌላው ደግሞ ደሳለኝ አራጌ የሚባለው የአንዷለም ወንድም የት እንዳለ ለቤተሰቡ ስለጠፋባቸው ፤አሜሪካን አገር የምትኖረው ዓይናለም የምትባለው እህቱ ስለ ወንድማቸው ሁኔታ ያጠያይቅ ዘንድ በጠየቀችው መሰረት አንዱዓለም፦ “ወንድሜ በህይወት አለ ወይ? የት ይሆን ያለው?” ብሎ ጓደኛውን ሲጠይቅ፤” በትግል ውስጥ ያለን ሰው ለምን ትጠይቃለህ? እሱ ለህይወቱ የሚያሰጋው ሥፍራ ላይ አይደለም” የሚል መልስ ተሰጥቶት አንብቤአለሁ”ብለዋል-ዶክተር ነጋሶ።
ሆኖም፤ የዚህ ዓይነት የመልዕክት ልውውጦች ሰዎችን ለእስር ማብቃታቸው አስገራሚ እንደሆነባቸው ዶክተር ነጋሶ አመልክተዋል።
ዶክተር ነጋሶ አያይዘውም፦“የተደራጀነው ልንቃወም ሆኖ ሳለ፤ አንዱዓለም በህዝብ ግንኙነት ኃላፊነቱ በርካታ ስብሰባዎች መምራቱን፤ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፓርቲያችን ጋብዞት ያቀረበውን ጽሑፍና የመራውን ሰብስባ የሽብር ተግባር አድርገው በማስረጃነት ፍ/ቤት አቅርበውታል፡፡ ናትናኤልንም፤ በት/ቤት ብጣሽ ወረቀት አቅርቧል ብለው ክስ መስርተውበታል”ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት በእንግሊዝ አገር የገበያ ማዕከል ለማቃጠል ሲሰናዱና ፈንጂ ሲያዘጋጁ የተያዙት ሰዎች በተራ ወንጀል እንጂ በሽብርተኝነት አልተከሰሱም ያሉት ዶክተር ነጋሶ፤ ኢህአዴግ ግን ከምንም ተነስቶ ምክንያት በመፈለግ ዜጐችን በሽብር ይከሳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በናትናኤል ላይ የተፈፀመበትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ለፍ/ቤት ሲያስረዳ መስማታቸውን ያስታወሱት የአንድነቱ ሊቀ-መንበር፤ ይሁንና እስካሁን ድረስ ኢ-ሰብአዊ ተግባሩ መቀጠሉንና እስረኞች የሚፈፀምባቸውን በደል ለፍ/ቤት ቢያመለክቱም፤ ፍ/ቤቱ ምንም ዓይነት መፍትሔ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጸዋል።
እነ አንዱዓለምን ለመጠየቅ ከሌሎች የትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ማረሚያ ቤት ቢሄዱም ፤ማረሚያ ቤቱ ሊያገናኛቸው ፈቃደኛ እንዳልሆነም ዶክተር ነጋሶ ተናግረዋል።
የአንድነቱ ሊቀ-መንበር በመጨረሻም፦ “እነ አንዱ ዓለም ለሠላማዊ ትግል መስዋዕት እየከፈሉ ናቸው፡፡ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ፤ሽብርተኝነት አይደለም፡፡ እስኪፈቱ ድረስ ይህ የሻማ ምሽታችን ይቀጥላል” ብለዋል፡፡
በሻማ ማብራት ዝግጅቱ ላይ የተለያዩ ግጥሞች ከመቅረባቸውም በላይ የአንድነት ፓርቲ መዝሙርም ተዘምሯል።