ሐምሌ ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢትዮጵያውያኑ ዛሬ በኖርዌይ የእንግሊዝ ኢምባሲ ፊት ለፊት ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ የአቶ አንዳርጋቸውን ተላልፎ መሰጠት በእጅጉ አውግዘዋል። ከፍተኛ ቁጣ ባስተናገደው ተቃውሞ እንግሊዝ እየወሰደችው ያለው እርምጃ እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል።
በኖርዌይ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ደግሞ በቅርቡ ከደቡብ ሱዳን ተይዘው ለኢህአዴግ የደህንነት አባላት ተላልፈው የተሰጡትን የአቶ ኦኬሎ አኳይን ጉዳይ በማንሳት ኖርዌይ መልስ እንድትሰጣቸው ጠይቀዋል።
የእንግሊዝ ኢምባሲ ተወካይ ሰልፈኞቹን ወጥተው ያነጋገሩ ሲሆን፣ እንግሊዝ አቶ አንዳርጋቸውን ለመጎብኘት ፈቃድ እንዲሰጣት ጥያቄ ማቅረቡዋንና መልስም እየጠበቀች መሆኗን መናገሩዋን የሰልፉ አስተባባሪ ግብረ ሃይል አባል የሆኑት አቶ ደባሱ መሰለ ገልጸዋል።
ኖርዌይ በበኩሏ የአቶ ኦኬሎን ጉዳይ በቅርብ ተከታትላ አስፈላጊውን መረጃ እንደምትሰጥ መግለጿን አስተባባሪው አቶ ዳንኤል አበበ ተናግረዋል
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቶ አንዳርጋቸውን በግፍ መታሰር አሁንም የህዝቡ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንደሆነ ነው። ኢህአዴግን በመረጠው መንገድ እንፋለማለን ያሉ ሰዎች የተለያዩ የተቃዋሚ ድርጅቶችን እየተቀላቀሉ ሲሆን፣ ግንቦት7ትን ለመቀላቀል የሚጠይቁ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው ከፍተኛ መሆኑን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የአቶ አንዳርጋቸው መታሰርን ትህዴን፣ አርበኞች ግንባር፣ አርዱፍና በጄ/ል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ ማውገዛቸው ይታወቃል። በሰላማዊ ትግል ከሚታገሉ ድርጅቶች መካከል ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ “የአቶአንዳርጋቸውፅጌሰብዓዊአያያዝእንዳሳሰበውና “ህወሓትመራሹየኢህአዴግአገዛዝአያያዛቸውንግልፅእንዲያደርግሰብዓዊክብራቸውምእንዲጠበቅበጥብቅ” ማሳሰቡ ይታወሳል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፕሪቶሪያ በሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ፊት ለፊት ማክሰኞቹ የተቃውሞ ሰልፍ የሚያደርጉ ሲሆን በሎስ አንጀለስ የእንግሊዝ ኮንስላ ጽ/ቤት ፊት ለፊትም በተመሳሳይ ቀን ተቃውሞ ይደረጋል።