ሰኔ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ሚሚ ስብሀቱ ፦”ጋዜጠኛው እኛን አይወክልም”በማለት ክደዋል። ጋዜጠኛው ቪዛ ያገኘበት መንገድ አነጋጋሪ ሆኗል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር ያለበትን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለማካሄድ ወደ ጆሀንስበርግ ባቀናበት ወቅት ነው የዛሚ ኤፍ ኤም አዲስ ጋዜጠኛ አብሮ እንዲሄድ የተደረገው:–በሮያል ባፎኬንግ ስታዲየም የተካሄደውን የባፋና ባፋና እና የዋልያዎችን ጨዋታ ከስፍራው እየተከታተለ ሪፖርት እንዲያደርግ ተብሎ።
ይሁንና ዛሚ ኤፍ ኤምን በመወከል “ለዘገባ ” ተብሎ የተላከው የጣቢያው ጋዜጠኛ እንዳልክ ባዬ ፤በዚያው የውሀ ሽታ ሆኖ ቀርቷል።
ከሁሉ አስገራሚው ነገር፤ በፌዴሬሽኑ ይሁኝታ ከቡድኑ ጋር ተጉዞ ጠፋ ስለተባለው ጋዜጠኛ ጉዳይ ከፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚዎች አንዳንዶቹ ምንም የሚያውቁት ነገር አለመኖሩ ነው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጊዜያዊ ወኪል አቶ ዳኛቸው ሳይቀሩ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነው የተናገሩት።
መጥፋቱን ከሰሙ በሁዋላ ግን ጉዳዩን በቅርበት መከታተል መጀመራቸውን ይናገራሉ።
የዛሚ ባለቤትና መሥራች የሆኑት ወይዘሮ ሚሚ ስብሀቱ ፦”በዛሚ ኤፍ ኤም 90 ነጥብ 7 ስም ሄዶ ስለጠፋው ጋዜጠኛ የምናውቀው የለም፤ ጋዜጠኛው የ እኛን ጣቢያ አይወክልም” በማለት ክደዋል።
ለዚህም የኢት ዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባቀረብንለት ጥያቄ መሰረት ጋዜጠኛ እንዳልክን በጣቢያው ስም እንዳልላከ የደብዳቤ ማረጋገጫ ሰጥቶናል ብለዋል-ወይዘሮ ሚሚ።
ይህን ተከትሎ የዛሚው ጋዜጠኛ እንዴት ከቡድኑ ጋር ሊሄድ ቻለ? በምን መንገድ ቪዛ ሊያገኝ ቻለ? የሚለው ጉዳይ በፌዴሬሽኑ ውስጥ ውዝግብ መፍጠሩ እና አነጋጋሪ እየሆነ መምጣቱ ታውቋል።
ወይዘሮ ሚሚ ፦” የጠፋው ጋዜጠኛ ጣቢያችንን አይወክልም” ቢሉም፤እንዳልክ ባዬ የዛሚ ጋዜጠኛ ከመሆኑ አንፃር ምላሻቸው ውሀ የሚቋጥር አይደለም ይላሉ-የፌዴሬሽኑ ሠራተኞች።
ችግሩ የፌሬሽኑ? የዛሚ ባለቤቶች?ወይስ የሁለቱም? የሚለው ጉዳይ ገና እየተፈተሸ ነው።
ዜናውን የተመለከቱ በርካታ አንባቢያን “ ለዘገባ ነው “በማለት በተወናበደ መንገድ ቪዛ እየወሰዱ የሚጠፉት ዛሚዎች ፤ራሳቸውን የጋዜጠኝነት ሙያ ጠበቃ ለማድረግ ሲሞክሩ መታየታቸው አስቂኝ ነው በማለት አስተ ዬት ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በዓለምና በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ ለሚገኙት ለኢትዮጵያ ሴቶችና ወንዶች ብሔራዊ ቡድኖች የገንዘብ ሽልማት ሰጥቷል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በሸራተን አዲስ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ለሴቶችና ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ለእያንዳንዳቸው አራት ሺሕ ብር ሸልሟቸዋል፡፡
አራት ሺህ ብር በወቅቱ ምንዛሬ ተመን መሰረት ከ 200 ዩሮ ጋር እኩል ነው።
በኢትዮጵያ የወቅቱ ገበያ መሰረት ደግሞ ፤ አንድ ጥሩ በግ ወይም ሦስት ኩንታል ጤፍ የመግዛት አቅም አለው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዘንድሮው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የእግር ኳስ ማጣርያ ውድድሮች ላይ እየተሳተፉ ለሚገኙት የኢትዮጵያ ሴቶችና ወንዶች ብሔራዊ ቡድኖች የቸርችል ሆቴል ቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ እንዳለ ገነሞ የእራት ግብዣ በማድረግ የሽኝት ፕሮግራም እንዳደረጉላቸው የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል፡፡
ትናንት ምሽት ወደ ዳሬ ሰላም ያመሩት የሴቶች ብሄራዊ በድን አባላት(ሉሲዎች) ነገ ቅዳሜ ከታንዛኒያ ጋር ይገጥማሉ፡፡
በተመሣሳይ ትናንት ምሽት ወደ ፖርቶ ኖቮ ያመሩት ዋልያዎች ደግሞ የፊታችን እሁድ ከቤኒን አቻቸው ጋር ይጫዎታሉ።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide