ኢሳት (ሚያዚያ 16 ፥ 2009)
በአዊ ዞን ቻግኒ ከተማ የባጃጅ ታክሲ አሽከርካሪዎች ዛሬ የስራ ማቆም አድማ ጀመሩ። ከትራንስፖርት ታሪፍ ጋር በተያያዘ አሸከርካሪዎቹ በመቱት አድማ፣ የቻግኒ ትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
የባጃጅ አሽከርካሪዎች የዋጋ ታሪፍ እንዲቀንስ በመንግስት የተወሰደውን ዕርምጃ ተከትሎ ነው የስራ ማቆም አድማውን የመቱት። ከ190 በላይ የባጃጅ አሽከርካሪዎች በተሳተፉበት በዚሁ ድርጊት፣ የቻግኒ ከተማ የታክሲ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ማድረጉን የደረሰን ዜና ያስረዳል።
ከዚህ ቀደም አስፋልት ባልሆኑ መንገዶች 2 ብር ይከፈል የነበረው አሁን የአስፋልት መንገድ ከተሰራ በኋላ ወደ አንድ ብር ዝቅ እንዲያደርጉ የተወሰነባቸው የባጃጅ አሽከርካሪዎች “ውሳኔው ተገቢ አይደለም ፥ ከናረው የነዳጅ ዋጋ አንጻር ታሪፍ መቀነሱ ለኪሳራ ይዳርገናል” በሚል ተቃውሞ ስራ ማቆማቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ይሁንና ጉዳዩ ከዚያ ያለፈ፣ በቅርቡ በአማራ ክልል ከአካሄደው ህዝባዊ ንቅናቄ ጋር የተገኛኘ እንደሆነ ይነገራል።
ምንም እንኳን የስራ ማቆም አድማው የታክሲ እገልግሎቱን ቢያቋርጡም፣ ህዝቡ አድማውን ከመቱት አሽከርካሪዎች ጎን መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። 5 የሚሆኑ ከስርዓቱ ጋር በጥቅም የሚገናኙ ባለሃብቶች አድማው ባለመቀላቀል ስራ ለመጀመር መንገድ ሲወጡ በህዝብ ተቃውሞ መመለሳቸው ታውቋል።
በአድማው የተደናገጠው የቻግኒ አስተዳደር እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ የትራፊክ ፖሊሶች የቆሙ ባጃጆችን ሰሌዳ በመፍታት አድማውን ለማስቆም እየሞከሩ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል። ይህ ዜና እስከ ተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎ እንደሚገኝ መረጃው ያመለክታል።