በትግራይ ምንነቱ ባልታወቀና በሽታ ሰው እያለቀ ነው

መጋቢት 3 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-በትግራይ ክልል ምንነቱ ባልታወቀና መድሀኒት ሊገኝለት ባልቻለ በሽታ ሰው እያለቀ መሆኑን አቶ አስገደ ገብረሥላሴ አጋለጡ። የክልሉ ጤና ቢሮ በሽታውን ማወቅ አልተቻለም ይላል።

የቀድሞው የህዝባዊ ወያነ ሀርነት  ትግራይ(ህወሀት)ታጋይና የአሁኑ የአረና ለትግራይ ፓርቲ አመራር አባል አቶ አስገደ እንዳሉት  ከ10 ዓመት በፊት  በመዳባይ ዘና ወረዳ  በምትገኝ አንዲት አነስተኛ ቀበሌ ውስጥ ተከስቶ ለብዙ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ይህ ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ፤ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ህዝብ ወደሚኖርባቸው ወረዳዎች እየተዛመተ ነው።

በወቅቱ በሽታው ሲከሰት ሪፖርት የተደረገላቸው በጊዜው የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ የነበሩት የአሁኑ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አቶ ቴዎድሮስ አድሀኖም ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋይ በርሄና ምክትላቸው የነበሩት አቶ አባዲ ዘሙ ፤ ነገሩን ችላ ስላሉትና ተቆርቁረው መፍትሔ ስላልሰጡት በሽታው ወደ ተለያዩ ቀበሌዎች ተስፋፍቶ  በ1998 ዓመተ-ምህረት በፃዕዳ ቀበሌ ብቻ ከ 250 የሚበልጡ ሰዎች በህመሙ ተጠቅተው  87ቱ መሞታቸውን አቶ አስገደ አስታውሰዋል።

አቶ አስገደ እንዳሉት፤የመንግስትም ሆነ የኢህአዴግ ሚዲያዎች ስለዚህ በሽታ መናገር የጀመሩት፤በሽታው ወደ አስገደ ፅንብላ፣ ታህታይ አድያቦ፣ ላዕላይ አድያቦ፣ ታህታይ ቆራሮ፣ ላዕላይ ቆራሮ (መደባይዘና)፣ ፀለምት እና አዴት ወረዳዎች ተዛምቶ 229  ከሞቱና ይህንኑ አስመልክቶ  የአቶ መለስ አማካሪ የነበሩት ዶክተር ገብረአብ በርናባስ መግለጫ ከሰጡ በሁዋላ ነው።

ከዚህም ባሻገር ጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ቴዎድሮስ አድሀኖም ስለዚህ ምንነቱ ስላልታወቀ በሽታ በሪፖርተርና በ አዲስ ነገር ጋዜጦች ለቀረበላቸው ጥያቄ፦”ይህ ነገር እኔን አይመለከተኝም። ዶክተር በርናባስን ጠይቁት”የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ያወሱት አቶ አስገደ፤ ሰብዓዊ መብት በሚከበርበት አገር ቢሆን የጤና ጥበቃ ሚኒሰትርን ያህል ባለሥልጣን 10 ዓመት ሙሉ ህዝብን እየገደለ ስላለ በሽታ ደብቄ አቆያለሁ ቢል በህግ ይጠየቅና ይፈረድበት እንደነበር አብራርተዋል።

 የትግራይ ክልል  ጤና ቢሮ በበኩሉ ይህን በሽታ ለማወቅና መድሃኒት ለማግኘት የበሽተኞችን ደም፣ ሽንት፣ ከአካላቸው  ለካልቸር ምርመራ የሚሆን ስጋ በመቁረጥ፣ እንዲሁም የአካባቢውን ዕፅዋት፣ የምግብ ሰብልና ውሃ ጭምር  ወደ አሜሪካና ጀርመን በመላክ ፤እንዲሁም   ከተለያዩ የውጭ ዩኒቨርሲቲ  ወደ ኢትዮጵያ ለምርምር በመጡ ሀኪሞች እዚሁ ቢያስመረምርም፤ ከሁሉም ምንም ውጤት እንዳልተገኘ ይናገራል።

 በመቀሌ  እና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተደረገውም የምርመራ ጥረት ምንም ውጤት ሊያሳይ እንዳልቻለ ቢሮው መግለጹን አቶ አስገደ ተናግረዋል።

የበሽታውን ምልክት አቶ አስገደ ሲያብራሩም፤ ታማሚዎቹ በመጀመሪያ ብርድ ብርድ ይላቸዋል። ከዚያም ሙቀት ይለቅባቸዋልል።በማስከተልም የ የዕብደት ምልክት ያሳያሉ።በመጨረሻም ሰውነታቸው በሙሉ ቀጭጮ ሆዳቸው ይነፋና ይሞታሉ።

“ያገራችን መሪዎች  ይህ በሽታ ከአቅማቸው በላይ ከሆነ፤ ለዓለማቀፍ ህብረተሰብ አስታውቀው የሰውን ህይወት ለማዳን መፍትሄ እንደመፈለግ፤ እጅግ ብዙ ህዝብ እንደቅጠል እየረገፈ ባለበት ሰዓት አፋቸውን ሞልተው ‘በአገራችን የህክምና አገልግሎት  ሽፋን 70 እና 80 በመቶ ደርሷል’ እያሉ ይደሰኩሩብናል። ይህ በእውነቱ ህዝብን ማታለል ነው”ይላሉ አቶ አስገደ ገብረሥላሴ።

በሽታው በ አሁኑ ጊዜ በማዕከላዊ ትግራይ ዞን፣በአክሱም፣በተምቤንና በአድዋ አውራጃዎች እንደታየ መረጋገጡን የጠቆሙት አቶ አስገደ፤  ከወዲሁ መፍትሄ ካልተፈለገለት ወደ ሌሎች ክልሎችና አህጉሮች ጭምር በመዛመት በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ እልቂት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide