ኢሳት (መስከረም 9 ፥ 2009)
ከታንዛኒያ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ በዝግጅት ላይ የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞች አውሮፕላን በአንድ የአማን ዜጋ ተሳፋሪ ሁከት ተፈጥሮበት በረራው መስተጓጎሉን የታንዛኒያ የጸጥታ ሃይሎች ሰኞ አስታወቁ።
በርካታ መገደኞች አሳፍሮ ወደ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ሊያቀና የነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን የአማን ዜጋ ተሳፋሪው እራሱን በመጸዳጃ ቤት በመቆለፍ አልወጣም ብሎ በማስቸገሩ በዳሬ ሰላም አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሮ ማርፈዱ ታውቋል።
የጸጥታ ህይሎች ድርጊቱ ከሽብርተኛ ጥቃት ጋር ሊገኛኝ ይችላል በሚል ተሳፋሪዎችን በማስፈረድ መንገደኛውን ለመያዝ የቻሉ ሲሆን በአውሮፕላኑ ላይ ጉዳት መድረሱን የታንዛኒያ የጸጥታ ሃይሎች ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በመንገደኛ አውሮፕላኑ ላይ ጉዳት አድርሷል የተባለው አሊ ታቢት አሊ በአሁኑ ሰዓት በቁጥጥር ስር ውሎ መገኘቱንና በአሮፕላኑ ላይ ለደረሰው ጉዳት ክስ እንደሚመሰረትበት በአቢየሽን ጉዳይ ዙሪያ የሚታተመው ቱርቦ ኒዎስ መጽሄት ዘግቧል።
የአማን ዜግነት ያለው መንገደኛው ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ትኬትን ገዝቶ የነበረ ሲሆን፣ በረራ ከመጀመሩ በፊት ባልተለመደ መልኩ ወደ መጸዳጃ ቤት መግባቱን የታንዛኒያ የጸጥታ ሃይሎች አስታውቀዋል።
ከ15 ደቂቃ በኋላ ከመጸዳጃ ቤቱ መውጣት የቻለው መንገደኛ የሆድ ህመም አጋጥሞት እንደነበር ቢገልጽም፣ የጸጥታ ሃይሎች ጥርጣሬ አድሮባቸው ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን የታንዛኒያ አቪየሽን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የሃገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ሁከትን ፈጥሮ የነበረው የኦማን መንገደኛ አውሮፕላኑ ለመጥለፍ ፍላጎት ሳይኖረው አልቀረም በሚል ተጨማሪ ምርመራ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ቱርቦ ኒውስ የደህንነት አባላትን ዋቢ በማድረግ በዘገባው አመልክቷል።
የታንዛኒያ የጸጥታ ሃይሎች ምርመራቸው ካጠናቀቁ በኋላ ግለሰቡ ከሃገር እንዲወጣ እንደሚደረግ ያስታወቀው መጽሄቱ በአውሮፕላኑ ላይ የደረሰው ጉዳትን በማወቅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማብራሪያ እንዲሰጥ እየተጠበቀ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ድርጊቱ በአየር ማረፊያውና በመንገደኞች ላይ ድንጋጤ ፈጥሮ ማርፈዱን የታንዛኒያው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ባለፈው አመት ከቻድ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ላይ በነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ አንድ የሱዳን ዜግነት ያለው መንገደኛ በአንድ እስራዔላዊ ድብደባ ፈጽሞ ተመሳሳይ ስጋት መፍጠሩ ይታወሳል።