በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች መታሰራቸውን መንግስት አመነ

ግንቦት ፰ (ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮምያ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት ተማሪዎችን አስሮ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ የኦሮምያ ፖሊስና የጸረ ሽብር ግብረሃይል በጋራ አስታውቀዋል።

በአለማያ ከደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘም እጃቸው አለበት ብሎ የጠረጠራቸውን ሰዎች መያዙን መንግስት ገልጿል።

አጠቃላይ ግጭቱን  የቀሰቀሱትን ሃይሎች ለመያዝም ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ከፖሊስ እና ጸረ ሽብር ግብረ ሃይሉ የተሰጠው መግለጫ፣ ቀደም ብሎ በአፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ ከተሰጠው መግለጫ ጋር ተቃራኒ ሆኖ ተገኝቷል። አቶ አባዱላ ችግሩን የቀሰቀሱትና ወደ ደም መፋሰስ ደረጃ የወሰዱት አሸባሪ ድርጅቶች ናቸው በሚል ግንቦት7ትንና ኦነግን ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወቃል። የኦሮምያ ፖሊስ እና የጸረ ሽብር ግብረሃይሉ ግጭቱን ያስነሱት ሃይሎችን ለማወቅ ገና ጥረት እያደረገ መሆኑን መግለጹ የአባዱላን መግለጫ ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።

አንዳንድ ወገኖች በተማሪዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት መንግስት ሆን ብሎ ያቀነባበረው ነው በማለት አስተያየት ይሰጣሉ፡

መንግስት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች መታሰራቸውን ቢያምንም የታሰሩ ተማሪዎችን ቁጥር እስካሁን ይፋ አላዳረገም። እስካሁን ባሉት መረጃዎች ከ1 ሺ በላይ የኦሮሞ ተወላጆች ታስረዋል። ከ50 አላነሱ ደግሞ በአጋዚ ጦር ተገድለዋል።

በክልሉ ያለው ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ። የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን የተቃወሙና ግጭት አነሳስተዋል ተብለው የተጠረጠሩ የኦህዴድ አባላት እየተፈለጉ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

የአለማቀፍ ተቋማትና በአገር ቤት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ገዳዮቹና ትእዛዙን የሰጡ ባለስልጣናት ለፍርድ እንዲቀርቡ እያሳሰቡ ነው።