(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 10/2011) በሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት የተጠረጠሩት ግለሰቦች በሚቀጥሉት 7ቀናት ክስ እንዲመሰረትባቸው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ።
ግለሰቦቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ለመደገፍ በመስቀል አደባባይ በተጠራው ትዕይንተ ህዝብ ላይ ቦምብ በማፈንዳት እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠትና ድርጊቱን በማቀነባበር እጃቸው አለበት የተባሉ ናቸው።
አቃቤ ሕግ ምርመራዬን አልጨረስኩም በማለት ተከሳሾቹን በማዕከላዊ ምርመራ ውስጥ ማቆየቱ ይታወቃል።
ሰኔ 16/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጀመሩትን የለውጥ ጉዞ በመደገፍ በመስቀል አደባባይ በተጠራው ትዕይንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የቦምብ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወሳል።
የቦምብ ጥቃቱን በማድረስ የተጠረጠረው ጥላሁን ጌታቸው ቦምብ ያፈነዱትን ሰዎች ጭኖ በራሱ ተሽከርካሪ መስቀል አደባባይ ያደረሰው ብርሃኑ ጃፋርና ድርጊቱን በማቀነባበር የተጠረጠሩት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ እስከ መስከረም 18 ክስ እንዲመሰረትባቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰቷል።
ተከሳሾቹ የጥቃት ሙከራው ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ በተደረገ ክትትል በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ላለፉት ሁለት ወራት ያህል በምርመራ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በብሔራዊ መረጃ ደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ የአንድ ክፍል ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ፣ድርጊቱን ያቀነባበሩት ካልተያዙ የበላይ አለቆቻቸውና ከሌሎች ግለሰቦች ጋር መሆኑን ፖሊስ መግለጹ ይታወሳል።
የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ መንግስት የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው ሲሆን የእስር ትዕዛዙ ከዚህ ጋር የተያያዘ ይሁን ይሁን አልታወቀም።
የቀድሞው ባለስልጣን ተላልፈው እንዲሰጡና የትግራይ ክልላዊ መንግስት ባለመፍቀዱ ወይንም እኔጋ የለም በማለቱ ሰውየውን ማሰር እንዳልተቻለም ታውቋል።