ጥቅምት ፲፬(አስራ አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቤይሩት ኢትዮጵያዊቷ በመኪና አደጋ ደርሶባት አስቸኳይ ህክምና ማግኘት ባለመቻሏ ህይወቷ አለፈ።
ኢትዮጵያዊቷ አስቸኳይ ህክምና ማግኘት ያልቻለችው- ቆንስላ ጽፈት ቤቱ ሀላፊነት አልወስድም በማለቱ እንደሆነ ተዘግቧል።
በዚህም ሳቢያ መዳን ስትችል የነበረችው ወጣት ህክምና ባለማግኘቷ ለህልፍት መብቃቷ፤ ዜናውን በማህበራዊ መገናኛዎች የተከታተሉትን ሁሉ አሳዝኗል።
የቆንጽላ ጽህፈት ቤት ሠራተኞች፤ ለግድብና ለተለያዩ ነገሮች እያሉ ኢትዮጵያውያኑ የሰው ፊት እያዩ ተንገላተውና ለፍተው ከሚያገኙት ገንዘብ መዋጮ ከመሰብሰብ ውጪ በእንደዚህ ዓይነት የፈተና እና የችግር ጊዜያቸው ዘወር ብለው እንደማያዩዋቸው በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
በዚህም ሳቢያ ገንዘብ ተበድረው ልጆቻቸውን ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚልኩ ኢትዮጵያውያን ወላጆች፤ እንደገና የልጆቻቸውን አስከሬን በብድር ገንዘብ የሚያስመጡበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።