ግንቦት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በዚሁ የዜና ዘገባ መሰረት በሰሜን ቤይሩት ግዛት ማስቲታ ጀቢል በተሰኘ ስፍራ የምትኖረው የ70 ዓመቷ አረጋዊት ወ/ሮ ሳሚያ፣ ድንቅነሽ የተሰኘች የ24 ዓመት ዕድሜ ያላት ኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛዋ፣ ከነሃስ በተሰራ ቅርፃ ቅርጽ ጭንቅላቷን ከመታቻት በኋላ የፈላ ውሃ ፊቷ ላይና ደረቷ ላይ በማፍሰስ ጉዳት አድርሳባታለች።
አደጋ የደረሰባት ግለሰብ ለህክምና በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል እንደተወሰደች የሚያትተው ይኸው ዘገባ፣ ፖሊስ የወንጀሉን መንስዔ ለማጣራት ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
በቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እሕቶቻችን በአሰሪዎቻቸውና በደላሎች እጅግ አስከፊ ግፍና በደል እንደሚፈፀምባቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ በተለያየ መንገድ ለሞትና ለአካል ጉዳት፤ እንዲሁም ለአዕምሮ ሕመም የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን እህቶች ቁጥራቸው እጅግ በርካታ እንደሆነ ይታወቃል።
እንግሊዝ አገር የሚታተመው ዘጋርዲያን የተሰኘው ጋዜጣ ከአንድ ዓመት በፊት እንደዘገበው ከሆነ በሊባኖስ ውስጥ ከ60-80ሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያዉያን በቤት ሰራተኝነትና በተመሳሳይ የስራ መስክ ተቀጥረው እንደሚያገለግሉ የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ ህጋዊ የሆኑት 43ሺህ ያህሉ ብቻ ናቸዉ