በቤንሻንጉል ክልል በተፈጠረ ግጭት ከ18 በላይ ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 21/2011) በቤንሻንጉል ክልል ማንዱራ ወረዳ ማምንኩክ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት ከ18 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።

የማቿቾች ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ ይችላል ተብሏል።

ፋይል

በሁለት ግለሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በተነሳው በዚሁ ግጭት ሰዎች ከመገደላቸው ሌላ ቤቶች ተቃጥለዋል ንብረትም ወድሟል ተብሏል።

የአማራ ክልል ሰላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ኮሌኔል አለበል አማራ ለኢሳት እንደገለጹት በግጭቱ የአማራና የጉምዝ ተወላጆች የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በአካባቢው ጥምር ሃይል ተሰማርቶ ችግሩ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ጥምር ሃይሉ ከቤንሻንጉልና ከአማራ ክልሎች እንዲሁም ከመከላከያ ሰራዊት የተውጣጣ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ኮለኔል አለበል አማረ እንደገለጹት በቤንሻንጉል ክልል ማንዱራ ወረዳ ባሉ ቀበሌዎች ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ 9 ሰዎች ታስረዋል።

ግጭቱ የተከሰተው በሁለት ግለሰቦች ጸብ ሳቢያ ቢሆንም አካባቢው እንዲተራመስ የሚፈልጉትና ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሰሩት በትግራይ የመሸጉ ሃይሎች እጅ እንዳለበት ምልክቶች አግኝተናል ብለዋል ኮለኔል አለበል አማረ።

እንደ ኮለኔል አለበል አማረ ገለጻ በጥቃቱ ከ18 በላይ ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ሁኔታው ከተጣራ በኋላ ደግሞ በጠቅላላ የተገደሉትንና የጉዳቱን መጠን በይፋ ለመግለጽ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

እስካሁን ድረስ ባለው መረጃም ከተገደሉት 18 ሰዎች መካከል ሌላ 4 ሰዎች ሲቆስሉ ቤትና ንብረትም ተቃጥሏል ነው ያሉት።

በቤንሻንጉል ክልል ማንዱራ ወረዳ ማምቡክ ከተማ አቅራቢያ ላለፉት 3 ቀናት የተፈጠረው ግጭት በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በአካባቢው በተሰማራው ጥምር ሃይል በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮለኔል አለበል ለኢሳት ገልጸዋል።

እንደእሳቸው አባባል ጥምር ሃይሉ ከቤንሻንጉል ጉምዝና ከአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች እንዲሁም ከመከላከያ የተውጣጣ ነው።

እናም ግጭቱ ካደረሰው ችግር በተጨማሪ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር መቻሉን ነው የገለጹት።

ይህ ግጭት 18 ሰዎች እስኪገደሉና ቤቶች እስኪቃጠሉ ድረስ ለምን ሁኔታውን ለመቆጣጠር ዘገያችሁ ለተባሉትም የሰው ሃይል እጥረት ስላለ ነው ብለዋል።

ወደ ፊት ግን እንዲህ አይነት ችግር ሳይደርስ ለመቆጣጠር ዝግጅት እንደሚደረግ ኮለኔል አለበል ቃል ገብተዋል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተደጋጋሚ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ለስደትና ለሞት ተዳርገዋል።