በፕሬስ ነጻነት ኢትዮጵያ አርባ ደረጃዎችን አሻሻለች

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 18/2011) በፕሬስ ነጻነት ኢትዮጵያ አርባ ደረጃዎችን ማሻሻሏን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት አስታወቀ።

የአሜሪካኑ ዋሽንግተን ፓስት ኢትዮጵያ ከዓመታት አፈና በኋላ ፕሬሱን ነጻ አደረገች ብሏል።

ሆኖም የፕሬስ ውጤቶቹ በሃገሪቱ ያለውን የብሔር ፍጥጫ እያባባሱት ነው ሲል ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ ገልጿል።

ሪፖርተርስ ዊዘአውት ቦርደርስ ባወጣው የ2019 የዓለም የፕሬስ ደረጃ ኢትዮጵያ አምና ከነበረችበት 150 ደረጃ ወደ 110 በመውረድ መሻሻል አሳይታለች ማለቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የ2019 የዓለም የፕሬስ ነጻነትን ደረጃ ይፋ ያደረገው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዘንድሮ የኢትዮጵያ ደረጃ በ40 መሻሻሉ ነው ይፋ ያደረገው።

ከ180 ሀገራት 110ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት ከሚጠቀሱ ሀገራት ቀዳሚውን ስፍራ መያዟን ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ ይፋ ባደረው ሪፖርት ተመልክቷል።

አምና 150ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ነበር በሪፖርቱ የተገለጸው።

በ2019 የሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደር መረጃ መሰረት ቻይና፣ ኤርትራ፣ ሰሜን ኮርያና ቱርኬሚስታን የመጨረሻዎቹን አራት ደረጃዎች በመያዝ የነጻ ፕሬስ ቀበኛ ተብለዋል።

ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ስዊዲን ኔዘርላንድና ዴንማርክ ደግሞ የፕሬስ ነጻነትን ሳይሸራረፍ እንዲከበር በማድረግ የመጀመሪያዎቹን አምስት ደረጃዎች መያዛቸው ተመልክቷል።

እንግሊዝ 33ኛ አሜሪካ ደግሞ 48ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ወዲህ የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት መሻሻል ማሳየቱን የገለጸው ደግሞ የአሜሪካኑ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ነው።

ለበርካታ ዓመታት በፕሬስ አፈና ውስጥ በቆየች ሀገር የተፈጠረው አዲሱ የነጻ ፕሬስ ለውጥ ተስፋና ስጋት ይዞ እንደመጣም ዋሽንግተን ፓስት በዘገባው አመልክቷል።

ነጻነቱ መረጋገጡን ተከትሎ ብቅ ያሉት ነባርና አዳዲስ የነጻ ፕሬስ ውጤቶች በሀገሪቱ አደጋ እያስከተለ ያለውን የጎሳ ግጭት እያባባሱት መሆኑን ጋዜጣው ገልጿል።

በሀገሪቱ የሚታየው የጎሳዎች ፍጥጫ ላይ የጋዜጦቹ ሚና አሉታዊ መሆኑን የጠቀሰው ዋሽንገተን ፖስት ጉዳዩ ኢትዮጵያውያንን አሳስቧቸዋል ሲል አትቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሄን ስጋት እንደሚጋሩ የጠቀሰው ዋሽንግተን ፖስት ነጻው ፕሬስ በሃላፊነት የማይንቀሳቀስ ከሆነ አደጋው ከባድ ነው ማለታቸውን ገልጿል።

በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽና የፕሬስ ነጻነት ጉዳይ መሻሻል ማሳየቱን በተመለከተ ሌሎች ዓለም ዓቀፍ ተቋማትም ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው።

በቅርቡ ሲፒጄ የተሰኘው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም ኢትዮጵያ አንድም ጋዜጠኛ በእስር ቤት የማይገኝባት ሀገር ሆናለች ሲል መግለጹ የሚታወስ ነው።