(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17/2011) በባሌ ዞን ሮቤና በጎባ ከተማ እየተበተኑ ያሉ የዛቻ ወረቀቶች በነዋሪው ላይ ስጋት መፍጠራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ።
በጽሁፉ ላይ መጤዎችን በማስወጣት የኦሮሞ ህዝብ ነጻነቱን በአካባቢው ላይ ለማስፈን ይሰራል የሚል እንደሚገኝበት የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የማስጠንቀቂያ ጽሁፍን የሚበትነው አባቶርቤ የተባለ ቡድን መሆኑንም የአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጠዋል።
በባሌ ዞን ሮቤና በጎባ ከተማ እየተበተኑ ያሉት የማስፈራሪያ ወረቀቶች ራሱን አባ ቶርቤ ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ።
በወረቀቱ ላይ ያለውም ጽሁፍ በአካባቢው ያለንው የኦሮሞ ተወላጆች እስካሁን ድረስ ለነጻነታችን ስንታገል ቆይተናል የሚል ጽሁፍ ሰፍሯል።
ይህንን ርምጃችንን ለማደናቀፍ በሚሞክር ማንኛውም ሃይል ላይ ደግሞ ርምጃ እንወስዳለን ሲል ማስፈሩ ደግሞ በነዋሪው ላይ ከባድ ጭንቀትን ፈጥሯል ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ባደረሱት መረጃ።
እንደ ነዋሪዎቹ አባባል ከሆነ ቄሮ በሚል የሚጠራው ሌላኛው ቡድንም በነዋሪዎች ላይ የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ሌላኛው ስጋት ሆኗል በአካባቢው ላይ ይላሉ።
በአካባቢው ለተፈጠሩትና ችግሮችን ህዝቡን ስጋት ላይ ለጣሉት ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ ህብረተሰቡን ለማወያያት የሚደረግ አንዳችም ጥረት የለም ይላሉ።
የአካባቢው ፖሊስና አንዳንድ ሃይሎች የተበተኑት ወረቀቶች ህብረተሰቡ ጋር ደርሰው የበለጠ ስጋትን እንዳይፈጥሩ ወረቀቶችን ከመሰብሰብ ውጪ ሌላ ነገር ሲያደርጉ አላስተዋልንም ብለዋል።
ነገር ግን የአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ነገሮችን ለማርገብ ያሰቡት ነገርም ሊሳካ የሚችል አይደለም ይላሉ።
ምክንያት አድርገውም የሚያስቀምጡት የሽማግሌዎቹም ሆነ የሃይማኖት አባቶቹ ደህንነትን አደጋ ውስጥ በመሆኑ ነው ይላሉ።
ነዋሪዎቹ ነገሮች ወደ ከፋ ደረጃ ከመሸጋገራቸው በፊት የሚመለከተው አካል ሊደርስልን ይገባል ሲሉ በኢሳት በኩል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።