በባለሀብቶች እንቅስቃሴ ባለመርካቱ መንግስት መሬት የመስጠቱን እንቅስቃሴ መግታቱን አስታወቀ

ሰኔ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሰፋፊ የግብርና መሬቶችን ለውጪ ባላሃብቶች በብዛት በመስጠቱ ምክንያት ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ወቀሳ እየቀረበበት የሚገኘው  የኢትዮጵያ መንግስት  ፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን የወሰዱ ባለሀብቶች እንቅስቃሴ አርኪ ባለመሆኑ መሬት መስጠት መግታቱን አስታወቀ።  ይሁን እንጅ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለባለሀብቶች ለመስጠት ዝግጅት መጨረሱን አስታውቋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ዛሬ የመ/ቤታቸውን የ2004 በጀት ዓመት የ10ወራት ሪፖርት ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት በግብርና ኢንቨስትመንት መሬት የወሰዱ የውጪ አገር ባለሃበቶች የሥራ አፈጻጸም መንግስታቸውን እንዳላሰደሰተ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ “ የውጪዎቹም ሆነ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችም፤ እኛ በምንፈልገው ፍጥነት ማልማት አልቻሉም” ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡ችግሩን ለመፍታትም ዓለም አቀፍ አጥኚ ባለሙያዎች ተቀጥረው በቀጣይ መንግስት መሬቱን አዘጋጅቶ በብዛት ለአልሚ ባለሃብቶች የሚያቀርብበት ሁኔታ እየተጠና ነው፡፡ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ መንግስት መቶ ሺ ወይንም ሁለት መቶ ሺ ሄክታር መሬት ለእርሻ ሥራ በሚመች መልክ እየከፋፈለ አዘጋጀቶ ፣መሬቱንም በብሎክ ከፋፍሎ ባለሃብቶች ሲመጡ በመስጠት በፍጥነት ወደ ልማቱ እንዲገቡ ታሰቦ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለመሬት ዝግጅት መንግስት ያወጣው ወጪ መሬቱ በሚተላለፍበት ወቅት ታስቦ ባለሃብቶቹ እንዲከፍሉ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡

መንግስት በአሁኑ ወቅት 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱን ሚኒስትሩ ጠቁመው በባለሃብቶቹ የስራ አፈጻጸም መንግስትን ባለማርካቱ የተጀመረው ጥናት እስኪጠናቀቅ መሬት የማሰተላለፉ ሥራ ጋብ እንዲል ተደርጓል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ መንግስት መሬት በገፍ በኢንቨስትመንት ስም ለባለሃብቶች የማደል ተግባሩ እንዲቆጠብ ያደረገው እሱ እንደሚለው የባለሃብቱ የስራ አፈጻጸም መድከም ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየበረታበት የመጣውን ተቃውሞ ለማረጋጋት በማሰብ መሆኑን በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው፡፡

አንድ ሰማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ ለኢሳት እንዳሉት ባለሃብቶች ሥራ የሚጀምሩት ሰርቶ  ለማትረፍ ነው፡፡ሥራቸውን በማዘግየት የሚጠቀም ባለሃብት የለም፡፡እናም ሥራቸውን በፍጥነት የሚሰሩት ለመንግስት ብለውም ሳይሆን ለራሳቸው ሲሉ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ከዚህ አኳያ ሲመዘን ሚኒስትሩ የሰጡት ምክንያት የሚያሳምን አይደለም ብለዋል፡፡

አያይዘውም የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሳይካሄድ፣የተፈጥሮ ሃብትን በሚጎዳና ገበሬዎችን የጥቂት ሐብታሞች ጭሰኛ በሚያደርግ መልኩ ተጧጡፎ የነበረው የመሬት ወረራ በአገር ውስጥ ባሉ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ሳይቀር በግልጽ የተቃወሙትና ድምጻቸውን ያሰሙበት ነው ብለዋል

የኢትዮጽያ መንግስት በተለይ በጋምቤላ አካባቢ ጠፍ መሬቶችን ከገበሬው እየነጠቀ ለሼህ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲን እና ለህንድ ኩባንያዎች አስተላልፏል በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚቀርብበት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡በቅርቡም በሼህ አልአሙዲን እርሻ ላይ የሚሰሩ የውጪ ዜጎች ላይ ሳይቀር ባልታወቁ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት  አራት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡

ሚኒስትር አቶ ተፈራ ለምን ያህል ባለሃብቶች፣ ምንያህል ሄክታር መሬት እንደተሰጠ ለፓርላማው የገለጹት ነገር የለም፡፡ሆኖም ሌሎች ምንጮች እንደጠቆሙት ከ800 ሺ ሄክታር መሬት በላይ ለባለሃብቶች መተላለፉንና ከዚህ ውስጥ መልማት የቻለው 17 በመቶ ያህል ብቻ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠው መሬት ለኢትዮጵያ ህዝብ ምንም የረባ ጥቅም እንደማያስገኝለት አለማቀፍ ጥናቶች ያመለክታሉ። አብዛኞቹ ባለሀብቶች መሬቱን በሄክታር 10 ብር እንዲገዙ፣ ለአምስት አመታትም ከታክስ ነጻ እንዲሆኑ እና መሬታቸውን ከ50 እስከ 99 አመት ለሚደርስ ጊዜ እንዲይዙ ይፈቀድላቸዋል። በእነዚህ እርሻዎች የሚፈናቀሉ ገበሬዎች ምትክ ቦታም ሆነ በቂ ካሳ ስለማይከፈላቸው ብዙዎች ለስደት ይዳረጋሉ። በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የመሬት ቅርምት አለማቀፍ ድርጅቶች ሳይቀር እያወገዙት ሲሆን አፍሪካዊያን ምሁራን ዳግም ቅኝ ግዛት እየተካሄደ ነው በማለት አስተያየት ይሰጣሉ። ባለሀብቶች የሚያመርቱት ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ የማይቀርብና በባለሀብቶች አገር የሚሸጥ በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ አገር በሚመረት ምርት የበይ ተመልካች ይሆናል ሲሉ ኦክላንድ ኢንስቲትዩትን የመሳሰሉ አለማቀፍ ተቋመት ይገልጣሉ።

የቤልጂየምን ግዛት የሚያክል መሬት ለውጭ አገር ባለሀብቶች ለመስጠት በዝግጅት ላይ የሚገኘው የመለስ መንግስት  እርምጃውን ካልገታ በአገሪቱ ውስጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ አስጠንቅቋል። በገዛ አገራቸው መሬት አልባ እየሆኑ የመጡትን አፍሪካዊያንን ለመታደግ በሚልም ተመድ አዲስ ህግ የመሬት ህግ ደንግጎ ይፋ አድርጓል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide