በቢሮአቸው ውስጥ ሞተው የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወ/ሮ አዲሴ ዘለቀ  የቀብር ስነስርዓት ተፈጸመ

ኢሳት (ህዳር 7 ፥ 2009)

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩትና በቢሮአቸው ውስጥ ሞተው የተገኙት ወ/ሮ አዲሴ ዘለቀ በተፋጠነ ሁኔተ የቀብር ስርዓታቸው መፈጸሙ ተነገረ።

የፓርላማ አባሏ በድንገት ሞተው ቢገኙም ምንም አይነት የአስከሬን ምርመራ ሳይደረግላቸው  ወደ ባህር ዳር ምሽቱን በመኪና ተወስደዋል።

የፓርላማ አባሏ ጠንከር ያሉ አስተያየቶችን በመሰንዘር ይታወቁ እንደነበር የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ሲታወጅ ከአማራ ክልል የተወከሉ ተመራጮች መቃወማቸው ይታወሳል። ከእነዚሁ መካከል ወይዘሮ አዲሴ አንዷ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።

የሁለት ልጆች እናት የነበሩት የፓርላማ አባሏ ወ/ሮ አዲሴ፣ በድንገተኛ ሁኔታ ማረፋቸውን የኢህአዴግ ድረገጽ ቢያስታውቅም የአስከሬን ምርመራ ስለመደረጉ ያለው ነገር የለም።

የ ወ/ሮ አዲሴ የቀብር ስነስርዓት ረቡዕ በተቻኮለ ሁኔታ መፈጸሙን ከባህር ዳር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አስከሬናቸው ከመቀበሩ በፊት ለቤተሰቦቻቸው በባህርዳር ከተማ ለሚታወቁ ሰዎች በጥይት ወይም በሌላ አለመሞቷን ተመልከቱ ተብለው እንዲያዩ መደረጉን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የብአዴን ታጋይ ከነበረው ሙሉዓለም አበበ ጀምሮ በርካታ በአገዛዙ ላይ ትችት ሲሰነዝሩ የነበሩ ሰዎች ተገድለው ይገኙ እንደነበር አይዘነጋም።

ከነዚሁም መካከል የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበረው ብርሃኑ የተባለ የብአዴን አባል በ ዲአፍሪክ ሆቴል በድንገት ሞቶ መገኘቱ አይዘነጋም።