በቡራዩ የፈረሰው መስጂድና በህዝቡ ላይ የተወሰደውን እርምጃ ኡዝታዝ አቡበክር አህመድ አወገዙ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ/ም) “በቡራዩ ከተማ በልዩ ስሙ አሸዋ ሜዳ ፍሪዶሮ “ፀበል ማዶ” ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ሙስሊሙ ሲገለገልበት የነበረው መስጂድ በታጠቁ የመንግስት ሃይሎች እንዲፈርስ መደረጉ ብሎም በንፁሃን የአካባቢው ሙስሊሞች ላይ የተወሰደው ኢ ሰብአዊ የሃይል እርምጃ ሃገራችን በአዲስ የለውጥ ጎዳና ላይ ገብታለች የሚለውን እሳቤ ጥላሸት የሚቀባና ሙስሊሙ ማህበረሰብ ይዞት የነበረውን የለውጥ ተስፋ የሚያጨልም ተግባር ነው፡” ሲሉ የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሊቀመንበር ኡስታዝ አቡበክር አህመድ ገልጸዋል።
ኡዝታዝ አቡበክር በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ፣ “ ዜጎች የፈለጉትን እምነት የመከተል፣እምነታቸውን የሚያራምዱበት ቤተ አምልኮ የመገንባት መብት ህገ መንግስቱ ቢደነግግም፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በአብዛኛው የሚገነባቸው መስጂዶች የጊዜ፣የአካል እና የህይወት መስዋትነቶችን እየተከፈለባቸው ነው” ብለዋል።
ኡስታዝ አቡበክር አክለውም “ሃገራችን በሰላም፣በእርቅ ፣በይቅርታ እና በመደማመጥ ላይ የተመሰረተ አንድነት ተፈጥሮ የሁሉም ማህበረሰብ ችግሮችን በመነጋገር እና በሰላማዊ መልኩ ለመፍታት ጥረት ይደረጋል በተባለበት በዚህ ወቅት፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የሃገሪቱ ግማሽ አካል ቢሆንም እስካሁን የሙስሊሙ ማህበረሰብን ቅሬታዎች ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ካለመታየቱ በተጨማሪ በአሸዋ ሜዳ የተከሰተው የመስጂድ ማፍረስ እና ሙስሊሙ ላይ ጥቃት የመፈፀሙ ተግባር መንግስት ለዘላቂ ሰላም እና ሃገራዊ መግባባት ሙስሊሙን ያማከለ ስራ እየሰራ አለመሆኑን “ የሚያመለክት ነው ሲሉ ቅሬታቸውውን ገልጸዋል።
“በቀደሙት አመታት በረመዳን ወራት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የተፈፀሙት ግፎች ቁስል ሳይደርቁ፣ ዘንድሮም የዚህን መሰሉ ተግባር በመንግስት ሃይላት መፈፀም መቀጠሉ በፅኑ የምናወግዘው ነው ያሉት ኡስታዝ አቡበክር ፣ “እንደ ሙስሊም ዜጋ በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት ያቀረብናቸው የመብት ጥያቄዎች በአዲሱ አመራር ምላሽ ይሰጥባቸዋል እንዲሁም ከሃይማኖት ነፃነት ጋር በተያያዘም እምነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እና ኢ ህገመንግስታዊ እርምጃዎች ይቆማሉ የሚል ፅኑ እምነት ሙስሊሙ ዘንድ አድሮ የነበረ ቢሆንም ከዚህ ቀደም የነበሩት የመብት ጥሰቶች በአዲሱ አመራር ጊዜም መቀጠሉም በቀጣይ የመንግስት አቋም ዙሪያ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርብን አድርጓል” ብለዋል።
“የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የአካባቢው ሙስሊም ማህበረሰብ መስጂዱን በተመለከተ ሊከተለው የሚገባውን ህጋዊ አካሄድ አሳውቀው ባለበት ወቅት ሌላ የመንግስት አካላት መስጂዱን በሃይል በመክበብ ምዕመናኑን በተከበረው የረመዳን ፆም ያለርህራሄ በመደብደብ እና አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ መስጂዱ በሃይል እንዲፈርስ፣ ቁርአኖች እንዲቃጠሉ እና ሙስሊሙን በገፍ እንዲታሰሩ መደተጉንም ኡስታዝ አቡበክር ገልጸዋል።
በቡራዩ ከተማ የተፈፀመው አሳዛኝ ተግባር እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጡ፣ባልታጠቁና በፆመኛ አንጀታቸው በመስጂዳቸው የሰላት ስነ ስርአት ሲፈፅሙ በነበሩ ሙስሊሞች ላይ ሴት፣ወንድ ህፃን ሳይለዩ አሰቃቂ ድብደባ የፈፀሙ አካላት ተገቢ የሆነ ማጣራት ተደርጎ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑናእና በፈረሰው መስጂድ ምትክም መንግስት ባስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ እንዲሁም ችግሮችን በሃይል እርምጃ ለመፍታት መሞከር በቅርብ አመታት ሃገራችን ለገባችበት አዘቅት ዋነኛ ምክንያት መሆኑ በተጨባጭ እየታየ አሁንም ይህን አካሄድ በሙስሊሙ ላይ ተግባራዊ እያደረጉ መቀጠሉ ሃገራችን ከገባችበት አለመረጋጋት የማያወጣት በመሆኑ መንግስት ባስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።