በቡሩንዲ የተካሄደው መፈንቅለመንግስት ውጤት አሁንም አልለየለትም

ፕሬዚዳንት ኑኩሩንዚዛ ለሶስተኛ ጊዜ ለመመረጥ መወሰናቸውን ተከትሎ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ መፈንቅለመንግስት ከተቀየረ በሁዋላ፣ አገሪቱ በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ በትክክል ለማወቅ አልተቻለም።
የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች ዋና ዋና የሚባሉትን ተቋማት በተለይም የሬዲዮ ጣቢያ፣ አየር መንገዱንና ቤተመንግስቱን በመቆጣጠር መፈንቅለ መንግስቱ እንደከሸፈ ቢያስታውቁም፣ መፈንቅለመንግስቱን የሚደግፉ ሃኢሎች በበኩላቸው፣ ተቋማቱ በእነርሱ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ እየገለጹ ናቸው።
መፈንቅለመንግስቱ ያልተሳካ መሆኑን የሚያመላክቱ ፍንጮች በመታየት ላይ ቢሆኑም፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለጉብኝት ከሄዱበት ታንዛኒያ ወደ አገራቸው ለመመለስ ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
በዋና ከተማዋ ውስጥ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ እየተሰማ ነው። መፈንቅለመንግስቱን በመደገፍ በርካታ ዜጎች ወደ አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ህብረትም ሆኑ ምእራባውያን ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ በመፈንቅለመንግስቱ ዙሪያ አስተያየት አልሰጡም።