ታኅሣሥ ፮ (ስድስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚገልጹት በጉጂ ዞን በቡሌ ሆራ ከተማ ከተለያዩ ቀበሌዎች እየተያዙ የሚታሰሩ አርሶአደሮች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ በቅርቡ ከተከፈቱት ሁለት እስር ቤቶች በተጨማሪ ሌሎች እስር ቤቶች መከፈታቸውንና እነሱም መሙላታቸውን ተናግረዋል።
ልጆቻቸውን የሚያጠቡ እናቶች፣ ወጣቶች፣ አዋቂዎችና በእድሜ የገፉ አዛውንት ሳይቀር መታሰራቸውን የሚገልጹት እነዚሁ ነዋሪዎች፣ በአሁኑ ሰአት አቅሙ ያላቸው ሰዎች አካባቢውን ለቀው መሰደዳቸውን፣ አቅሙ የሌላቸው ግን ከፍተኛ ድብደባ እየተፈጸመባቸው በመታሰር ላይ ናቸው።
ህዝቡ በከተማው ተነስቶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ የወደሙ ንብረቶችን እንዲተካ እየተገደደ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል። የሚታሰሩ ዜጎች በቤተሰቦቻቸው እንዳይጎበኙ በመደረጉ ስላሉበት ሁኔታ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል። እሱ ከአካባቢው በመሰወሩ በመያዣነት ባለቤቱ የታሰረችበት ግለሰብ እንዳለው፣ የባለቤቱ ዘመዶች ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ስለባለቤቱ ሁኔታ ለማወቅ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። ከቡሌ ሆራ በተጨማሪ በምእራብ አርሲ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች አፈናው ተጠናክሮ ቀጥሎአል። በክልሉ እስከ 50 ሺ የሚደርሱ ዜጎች ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ ታስረዋል ተብሎ ይገመታል።
በሌላ በኩል የቀድሞው የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ አፈጉባዔ እና የፓርላማ አባል ወ/ሮ አና ጎሜዝ የአውሮፓ ኅብረት ዓመታዊ የአገራት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ በተደረገ ውይይት የኢትዮጵያ መንግስትን ኢሰብዓዊነትነት እና አንባገነናዊ በማውገዝ ሕብረቱ ለኢትዮጵያ ልማት የሚመድበውን በጀት በድጋሜ እንዲያጤነው ጠይቀዋል።
”የአውሮፓ ኅብረት ምክርቤት ከሶስተኛ ዓለም አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጤን አለበት።በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ የአውሮፓ ኅብረት ያለውን ዝምታ ሊያቆም ይገባል።በቅርቡ የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪል የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና የሕዝባቸውን እና አገራቸውን ጉዳይ አስመልክቶ ውይይት ለማድረግ እዚህ በመምጣቸው ታስረዋል። በእስር ቤት ውስጥ ከጠበቃቸው ጋር እንዳይገናኙ ተደርገው ሰቆቃ ቶርቸር እየተፈጸመባቸው ነው። ዶ/ር መረራን በሽብር ለመከሰስ ያበቃቸው ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ጋር ተገናኝተው ውይይት በማድረጋቸው ነው። እነሱንም በሽብር ከሰዋቸዋል። እውነተኛው አሸባሪ ግን የኢትዮጵያ መንግስት ነው”ብለዋል።
ዶክተር መረራ ጉዲና ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች እንዲፈቱ የአውሮፓ ኅብረት ተጽእኖ እንዲያሳድር ሲሉም ወ/ሮ አና ጠይቀዋል። በአፍሪካ ውስጥ ለልማት እርዳታ ከሚሰጣቸው አገራት ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ተርታ መሆኗን ያወሱት ወ/ሮ አና፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕዝባቸውን በማፈን ሰቆቃ ለምትፈጽም አገር የገንዘብ እርዳታ ማድረግ ተገቢ አይደለም ሲሉ ተሟግተዋል።
”በኢትዮጵያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች በግፍ ታስረዋል፣ ተገለዋል፣ እስር ቤቶች በጋዜጠኞች ተጨናንቀዋል። ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆነው መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን እንዳያሰሙ እያደረገ ነው። ኢትዮጵያዊያን በዚህ ግፈኛ ስርዓት ተማረው ፈልሰዋል። በዚህ ዓመት ብቻ 88 ሽህ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በእርስበርስ ጦርነት ወደምትታመሰው የመን ባሕር አቆራርጠው ገብተዋል። ከእነዚህ ስደተኞች ውስጥ ሕይወታቸውን ያጡም አሉ። ምንያህል ኢትዮጵያዊያን እስኪሞቱ እንጠብቃለን? ኢትዮጵያ ወደ ማያባራ የእርስበርስ ጦርነት እስክትገባ ለምን እንጠብቃለን? የአውሮፓ ኅብረት ይህን አስቀያሚ አንባገነን ስርዓት እስከመቼ በዝምታ ይመለከታል?” በማለት በአንባገነኑን የህወሃት ኢህአዴግ ስርዓት ላይ የአውሮፓ ኅብረት የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።