(ኢሳት ዜና–ሕዳር 26/2010)
በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ዛሬ ህዝባዊ ተቃውሞ ተካሄደ።
በአጋሮ ተማሪዎች አደባባይ ወተው የህወሀትን መንግስት አውግዘዋል።
በባሌ ሮቤ መምህራን ተቃውሞ አሰምተዋል።
በቦረና ዞን የሰላማዊ ሰው ግድያ እንዲቆም በመጠየቅ ሰልፍ ተደርጓል።
በሀረር እስር ቤት በተነሳ ቃጠሎ በርካታ እስረኞች መጎዳታቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል በደቡብ ኦሞ በሙርሲ ታጣቂዎች 13 ሰዎች መገደላቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል ዛሬም የህዝብ ንቅናቄ በበርካታ ከተሞች መደረጋቸውን ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች አመልክተዋል።
በአጋሮ ዛሬ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ እንዲሁም በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ግድያው እንዲቆም ጠይቀዋል።
የአጋሮ ከተማ ነዋሪ በተቀላቀለበት በዚሁ ተቃውሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው እንግልት እንዲያበቃ ጥያቄ ቀርቧል።
በባሌ ሮቤ መምህራን አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን በመምህራን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና በደሎች እንዲቆሙ መጠየቃቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የመምህራን ደሞዝ እንዲስተካከልና መብቶቻቸውም እንዲከበሩ የጠየቀው የባሌ ሮቤው ሰልፍ በከተማዋ ነዋሪዎች ድጋፍ ማግኘቱ ተመልክቷል።
የሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ግጭት እስከአሁን መቆም ባልቻለበት ቦረና ዞን ህዝቡ የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄደ ሲሆን መንግስት ግድያውን የማያስቆም ከሆነ ራሱን ለመከላከል ርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
በቦረና እስከሞያሌ ድረስ አሁንም ውጥረት የነገሰ ሲሆን በየዕለቱ ሰዎች እንደሚገደሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በቦረናው ትዕይንት የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ኦህዴድ ላይም ተቃውሞ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል።
በሀረርጌ ጭናክሰን በተመሳሳይ የሶማሌ ልዩ ሃይል ግድያ እንዲያቆም የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።
በሌላ በኩል በሀረር ወህኒ ቤት ውስጥ በተነሳ ቃጠሎ በርካታ እስረኞች መጎዳታቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በከተማዋ ዋና ወህኒ ቤት የተነሳውን ቃጠሎ ተከትሎ፣ በእስረኞችና በፖሊሶች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በርካታ እስረኞች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
እስካሁን ባለው መረጃ 50 የሚሆኑ እስረኞች በቃጠሎው ጉዳት ሲደርስባቸው አንድ እስረኛ ህይወቱ ማለፉ ታውቋል። ቃጠሎው በምን ምክንያት እንደተነሳ የታወቀ ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ኢትዮጵያ በደቡብ ኦሞ ዞን በጂንካ ሃና ሙርሲ መስመር ላይ በሙርሲ ታጣቂዎች በርካታ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው አንድ የሙርሲ ተወላጅ በመኪና መገጨቱን ተከትሎ፣ የሙርሲ ተወላጆች ወደ አካባቢው ለስራ በሚንቀሳቀሱ ሹፌሮች ላይ በወሰዱት ጥቃት ከ13 ያላነሱት ህይወታቸው ሲያልፍ 24 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ ከጅማ ወደ ሙርሲ የሚወስደው መስመር ተዘግቷል። ኢሳት የጉዳቱን መጠን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን በመሰብሰብ ላይ ነው።