ኢሳት (ሰኔ 5 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ደርሶ ከነበረው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ጋር በተገናኘ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ያጡና ጉዳት የደረሰባቸው ከ20 በላይ ሰዎች ቃል የተገባላቸው ድጋፍ ተጓትቶብናል ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ።
የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ 23 የሚሆኑት ሰዎች በስፍራው ይኖሩ ስለመሆናቸው አስፈላጊውን መረጃ አሟልተው እንዲመጡ መታዘዛቸውን ገልጿል።
ከአደጋው የተረፉት እነዚሁ ቅሬታ አቅራቢዎች ጉዳቱ ከደረሰና የተለያዩ አካላት ገንዘብ ከለገሱ ሶስት ወራት ቢያልፍም፣ የተገባላቸው ድጋፍ ሊሰጣቸው አለመቻሉን በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በቅርቡ ተጎጂዎቹ የተገባልን የድጋፍ ቃል ተግባራዊ አልተደረገም ሲሉ ቅሬታን ማቅረባቸው ይታወሳል።
የከተማዋ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች መረጃ 94.5 ሚሊዮን ብር ከተለያዩ አካላት መሰብሰቡን እሁድ አስታውቋል። ህጋዊ ይዞታ ለነበራቸው 13 ሰዎች መሬትን ጨምሮ በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል ሲሉ የቢሮው ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና ሃላፊው ለሰዎቹ ምን ያህል ገንዘብ እንደተሰጣቸው የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም። እንዲሁም በቦታው ተከራይተው ይኖሩ ከነበሩት 54 ግለሰቦች መካከል ለ35ቱ የ10/90 ኮንዶሚኒየም ቤት የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አቶ ኤፍሬም አክለው አስረድተዋል።
ከሌሎች 102 ግለሰቦች መካከል ደግሞ ለ76ቱ የመኖሪያ ቤትና ግዢ የገንዘብ ዕርዳታ እንደተሰጣቸው የከተማዋ ሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ገልጿል።
ቢሮው ለሰዎቹ የገንዘብ ድጋፍና ቤት መስጠቱን ቢገልፅም የገንዘቡ መጠንም ሆነ የቤቱ አይነት በተመለከተ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
ድጋፍን ለማግኘት አስፈላጊውን መረጃ አሟልታችሁ አምጡ ከተባሉት 23 ሰዎች በተጨማሪ ሶስት አቤቱታ አቅራቢዎች በቦታው አለመኖራቸው ተረጋግጧል ተብሎ ከድጋፍ መሰናበታቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ከአደጋው የተረፉት አቤቱታ አቅራቢዎች ተሰጥቷቸዋል የተባለ የመኖሪያ ቤትም ሆነ ገንዘብ በእጃቸው እንዳልገባ በቅርቡ ቅሬታን ሲያቅረቡ ቆይቷል።
ለተጎጂዎች ተሰጥቷል የተባለ የመኖሪያ ቤት ግንባታው ያልተጠናቀቀ መሆኑን የሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ አቅርቦ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
በአካባቢው ደርሶ በነበረው አደጋ ከ 100 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸውንና በርካታ ነዋሪዎችም ያለመጠለያ መቅረታቸው የሚታወስ ነው።
ከአደጋው የተረፉት የአካባቢው ነዋሪዎች ለአደጋው መንግስትን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፣ የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው የቆሻሻ ክምሩ የተናደው የአካባቢው ነዋሪዎች ቁፋሮን በማካሄዳቸው ነው ሲሉ አስተባለዋል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት መንግስት ነዋሪዎቹን ከቆሻሻ ክምሩ እንዲነሱ አለማድረጉ እና ተቋርጦ የነበረውን ቆሻሻ በቦታው የመጣሉ ስራ እንዲቀጥል ማድረጉን ተገቢ አለመሆኑን ሲገልፁ ቆይተዋል።