ሮያል ስፖንጅ ፋብሪካ ለሦስተኛ ጊዜ ተቃጠለ
ሰኔ ፭ ( አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኮልፈ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ ካራቆሬ በሚባለው አካባቢ ዘይት ቤት በመባል በሚጠራው ግቢ የሚገኘው ‹‹ሮያል ስፖንጅ ፋብሪካ ›› ከጥቅምት 05/09 ጀምሮ እስከ ሰኔ 3 ቀን 20099 ዓ.ም ድረስ ባሉት 9 ወራት ለሦስተኛ ጊዜ መቃጠሉን ዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ከቀኑ 8 ሰዓት ተኩል ባልታወቀ ምክንያት የተነሳው እሳት የፋብሪካውን የምርት መጋዝን ሙሉ በሙሉ አጋይቶ ከፋብሪካው ድንበርተኛ የሆነ ወፍጮ ቤት አውድሞ በራሱ ጊዜ እየጠፋ ባለበት ሰአት ፣ የእሳት አደጋ መኪና 9 ሰዓት ተኩል አካባቢ ደርሷል፡፡ ባለፈው በተነሳው ቃጠሎ ከምርት መጋዝኑ በተጨማሪ የፋብሪካው ጄኔረተርና በድንበር የሚገኝ ወፍጮ ቤት ከመውደማቸው ሌላ፣ እሳቱ እንደከዚህ በፊቱ የጥቅምት 5 ቃጠሎ በንብረት ላይ የከፋ ውድመት ያለማስከተሉን ገልጸው በአካባቢው ህዝብ ላይ ከፍተኛ የመሸበር ስሜት እንደፈጠረ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በቃጠሎው ቦታ በአጭር ጊዜ ቁጥሩ በብዙ መቶዎች የሚቆጠር ህዝብ መገኘቱም ጠቅሟል፡፡
በስፍራው የነበረ ተባባሪ ሪፖርተራችን እንደገለጸልን በቃጠሎው ሰዓት ‹‹ የአካባቢው ነዋሪዎች ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋዊያን የሥነ ልቡና ችግር ውስጥ በመውደቃቸው፣ ‹እሳት › ሲባል ቤታቸውን ለቀው በመሸሽ አቅራቢያው ወደሚገኘው ኮንዶሚኒዬምና ገብርኤል ቤተክርስቲያን ድረስ መሄዳቸውን መመልከቱን ፣ እንዲሁም ነዋሪዎች “ፋብሪካው የራሱ የእሳት መከላከያ እንዴት አይኖረውም ? ካለው ማምረቻው ምንም ባልተነካበት እንዴት በቀን የተነሳውን እሳት መከላከል /ማጥፋት አልቻለም ? እስከመቼ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እየተሳቀቅን እንኖራለን ? መንግስት ስለእኛ ደህንነት ማሰብና አንዳች የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ አልቻለም ? አንድ ባለሃብት ከእኛ ይበልጣል ወይ ?” በማለት ጥያቄዎችን ሲያነሱ ነበር ብሏል፡፡
ጥቅምት 5/09 ተከስቶ በነበረው ቃጠሎ ከፋብሪካው ግቢ ውጪ ያሉ በርካታ መኖሪያ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር ያስታወሱ ነዋሪዎች ፣ ፋብሪካው ለነዋሪው ሰቆቃ ከማትረፍ ውጪ ነዋሪው አንዳችም ከፋብሪካው ያገኘው ጥቅም እንደሌለ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ቃጠሎውን ሰምተው በቦታው የደረሱትና ህዝቡ የሚናገረውን ብሶት ያደመጡት የፋብሪካው ባለቤት ናቸው የተባሉ ግለሰብ በብስጭትና በሃዘን ስሜት ‹‹ በእንዲህ አይነት ሁኔታ በየጊዜው ንብረትና ሃብታችን እየጋየና እየወደመ ልንቀጥል አንችልም፣ በቅርብ ጊዜ ለቀን እንሄድላችኋለን ፡፡›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡