ህዳር ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-34 የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ህገ-መንግስቱን በመጣስ ሶስት ጠ/ሚኒስትሮች በሾሙት በ/ጠ/ሚ/ር ሀ/ማርያም ደሳለኝ፣ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤትና ሹመቱን በተቀበሉት ሶስቱ ም/ጠ/ሚኒስትሮች ላይ ክስ ሊመሰረት መሆኑን ገልጠዋል።
ተሾሚዎቹም ቢሆኑ ሹመቱን መቀበል የለባቸውም ነበር ያሉን መግለጫውን አስመልክተን ያናገርናቸው ያስተባባሪ ኮሚቴው ፀሀፊ አቶ ግርማ በቀለ ህገ-ወጥ መሆኑን እያወቁ በመቀበላቸው ተከሳሾች ኛቸው ብለዋል።
በሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላት ላይ የተመሰረተው ክስ አግባብ አይደለም ያሉት የ34 ተቀዋሚ ፓርቲ ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ፀሀፊ አቶ ግርማ በቀለ በዚህና በአዲስ አበባ ከተሞች በሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ ቤታቸውን በማፍረስ የመኖር መብታቸውን መንግሰት በመጣሱ እንቃወመዋለን እዚህ ላይም እየሰራን ነው ብለዋል።
መንግስት ሁሉንም በእኩል የማስተዳደር ሀላፊነት እንዳለበት የገለፁት አቶ ግርማ ከዚህ በፊት ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች አልመለሱልንም ለዚህም በተለየ አግባብ ለጥያቄያችን መልስ ለማግኘት እንሰራለን ሲሉ አስታውቀዋል።