በቄለም ወለጋ ወረዳ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ኦነግ እንደሆኑ የሚገልጹ ወታደሮች ነዋሪዎችን የግል የጦር መሳሪያዎችን እንዲያስረክቡና ገንዘብም እንዲሰጡ እያስገደዱ ነው
( ኢሳት ዜና መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ/ም ) ኢሳት ያነጋገራቸው በቄለም ወለጋ ደምቢዶሎ አካባቢ ፣ በሰዮ ወረዳ፣ ወልጋይ፣ ቢቢካና ቀስሪ መንደሮች የሚኖሩ በ1977 ድርቅ ወቅት ከወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ሄደው የሰፈሩና በአካባቢው ለአመታት የኖሩ ዜጎች ፣ በአካባቢው የሚንቀቀሳቀሱ ወታደሮች፣ “ከአሁን በሁዋላ አካባቢውን የሚያስተዳድረው ኢህአዴግ ሳይሆን እኛ ነን፣ ኢህአዴግን አናውቀውም፤ የግል የጦር መሳሪያ ያላችሁ፣ መሳሪያችሁን አስረክቡ፣ ገንዘብም ክፈሉ” እያሉ እንደሚያስገድዱዋቸው ገለጸዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የቀበሌ አስተዳደሩን የኦነግ ታጣቂዎች ተረክበው እየሰሩ ሲሆን፣ የኦዴፓ መሪዎች በአካባቢው ባለመኖራቸው የደህንነት ስጋት ገጥሟቸዋል። መንግስት እውቅና ሰጥቶን ለረጅም ጊዜ የታጠቅነውን የነፍስ ወከፍ መሳሪያ አስርከቡ መባላቸውን የተቃወሙት ነዋሪዎቹ፣ መንግስት ፈቅዶ የታጠቅነውን መሳሪያችሁን አስረክቡ ቢለን ለማስረከብ ፈቃደኞች ነን ብለዋል። የኦነግ ወታደሮች ህዝቡን እየሰበሰቡ ኢህአዴግ እንደማያውቁትና ማንኛውንም ነገር ለኦነግ ወታደሮች እየነገሩ መፍትሄ እንደሚያገኙ እየተናገሩ መሆኑንም ያነጋገርናቸው በርካታ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ የመንግስት ሹም አለመኖሩን፣ ትናንት ምሽት የቀበሌውን አስተዳደሪ ይዘው በመምጣት መሳሪያ አላችሁ ወይ እያሉ ሲጠይቁ ማምሸታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የኦዴፓ የገጠር ዘረፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ኦነግ ትጥቁን ካልፈታ መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ መጻፋቸው ይታወቃል። ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ትናንት ፓርላማውን ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግርም፣ መንግስት ህግን ለማስከበር ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀመር ገልጸዋል። የኢህአዴግ ጉባኤ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድን በድጋሜ መሪ አድርጎ በመረጠበት ወቅት ጠ/ሚኒስትሩ ባሰሙት ንግግር መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።
ለኢሳት የሚደርሱት መረጃዎች እንዲያመለክቱት በቦረናና በጉጂ ዞኖች በኦነግ ስም የሰራዊት ምልመላ ስልጠና ይሰጣል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የኦነግ ወታደሮች ፍርድ ቤቶችን ተክተው ፍርድ እየሰጡ ነው።
የኦነግ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ ትጥቅን መፍታት በተመለከተ ለዋልታ ቴሌቪዥን የሰጡት ቃለምልልስ ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥሮ ነበር። ድርጅታቸው ቆይቶም ቢሆን ቃለምልልስ ከአውዱ ውጭ ተተርጉሟል በማለት ማብራሪያ ሰጥቷል።
በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው ኦነግ ጋር ያላቸው ግንኙነት እስካሁን ግልጽ አይደለም።
በሌላ በኩል ከቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ እና በምዕራብ ወለጋ ቢላ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በቂ እርዳታ ባለማግኘታቸው ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል። ተፈናቃዮቹ በአካባቢው የተጠናከረ አስተዳደር ባለመኖሩ እርዳታ ለማግኘት መቸገራቸውንና እርዳታ ለማግኘት ጥያቄ ሲያቀርቡ ከጠባቂዎች ጋር በሚፈጠር አለመግባባት የሰው ህይወት እያለፈ መሆኑን ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳውን አስተዳደሪ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።