የምርጫ ሕግ ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ ለውይይት ቀረበ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 29/2011) የኢትዮጵያን የምርጫ ሕግ ለማሻሻል የተዝዘጋጀው ረቂቅ ሕግ ለውይይት ቀረበ።

የምርጫ ቦርድ አባላት ከተቃዋሚዎችና ከገዢው ፓርቲ በእኩል መጠን ይሳተፉበታል የተባለው ረቂቅ ሕግ ቅሬታዎችን የሚያስተናግድ የምርጫ ፍ/ቤት እንደሚቋቋም ያስረዳል።

የፍርድ ቤቱ ተግባር ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚመረምርና ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነም ተመልክቷል።

አዲስ የተረቀቀውና ለውይይት የቀረበው የምርጫ ሕግ ማሻሻያ ሰነድ የሃገሪቱን የምርጫ ስነ-ስርዓት መቀየርን ጭምር ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተገኘው መረጃ ያመለከታል።

የሃገሪቱን የምርጫ ስርዓት ለመለወጥ ሕገ-መንግስቱን ማሻሻል ጭምር እንደሚያስፈልግ የታወቀ ቢሆንም የቀረበው ረቂቅ ሕግ እስከ ሕገ-መንግስት ማሻሻያ የዘለቀ እንደሆነም ተመልክቷል።

እስከ አሁን ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ተካሄዱ የተባሉት ምርጫዎች በአብላጫ የምርጫ ስርዓት የተካሄዱና በሕገ-መንግስቱ የተቀመጠው የምርጫ ስርዓት ይህ ቢሆንም በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ተመጣጣኝ ውክልና በተባለው የምርጫ ስርዓት በአማራጭነት ቀርቧል፣

የምርጫ ቦርድ አባላትን ከ9 ወደ 15 ከፍ የሚያደርገው ይህ ረቂቅ ሕግ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይሆን በራሱ በቦርዱ አባላት እንደሚመርጥም በረቂቅ ሕግነት ቀርቧል።

የምርጫ ቦርድ አባላቱ ከተቃዋሚ አራት እንዲሁም ከመንግስት አራት እንዲሁም ከሲቪክ ተቋማት 2 በአጠቃላይ 10 ሰዎች ይመረጡና አስሩ በጋራ ተጨማሪ 5 በስምምነት እንደሚመርጡም ታውቋል።

ለመራጭነት በምርጫ አከባቢው 6 ወር መኖር የሚለው ወደ አንድ ዓመት ከፍ ማለቱም ተመልክቷል።