ግንቦት ፲፫ (አስራ ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም ሊከናወን የታቀደው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከፋይናንስ አቅም ፣ከሰለጠነ የሰው ኃይል እና ከመሠረተ ልማት አለመሟላትና ከመሳሰሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ፈተናዎች ገጥመውታል፡፡
በዕቅዱ ዓመታት 11 በመቶና ከዚያ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የታሰበ ቢሆንም ባለፉት ሶስት የዕቅዱ ዓመታት የተመዘገበው እድገት 10 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ከኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ አንጻር በሚጠበቀው አቅጣጫ እና በጎላ መልኩ ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን መረጃው ይጠቅሳል፡፡
በተለይ ባለፉት ሶስት ኣመታት ካጋጠሙ ፈተናዎች መካከል በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት የተከሰተው የዋጋ ንረት፣ የግብርና ዘርፍ ምርታማነት ዕድገት አርኪ አለመሆን፣ ኤክስፖርት የገቢ ድርሻ ማሽቆልቆል ፣ የኢምፖርት ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ ማደግ፣ የግብርና ዘርፍ የምርታማነት ዕድገት የተፈለገውን ያህል አለመሆን፣ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከመነሻው መሠረተ ጠባብ መሆን፣ የግል ባለሃብቱ ተሳትፎ ማሽቆልቆል ፣ ከምንም በላይ የማስፈጸም አቅም ማነስ እና በየደረጃው የሙስናና ብልሹ አሰራር ፣የመልካም አስተዳደር ችግሮች መንሰራፋት ይጠቀሳሉ፡፡
የመካከለኛና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ልማት በውጪ ንግድ የሚመራ፣ የውጪ ምንዛሪ እጥረትን የመቅረፍና ለግብርና ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከተቀመጡ ኣላማዎች አኳያ ባለፉት ሶስት የዕድገትና የትራንስፎርሜሸን ዕቅድ የትግበራ ዓመታት ክንውን ወደኃላ የቀረ መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መረጃ ይጠቅሳል፡፡
በፕሮጀክቶችም ደረጃ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት መረጃ መጠናቀቅ የቻለው 30 በመቶ ያህል ብቻ ሲሆን በባቡር ፤ በስኳር፣ በማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ የተያዙ ዕቅዶች ቀጣዩ የእቅዱ መጨረሻ ኣመት ድረስ የሚሳኩ አይደሉም፡፡
በዚህም ምክንያት ለመጪው ዓመት ምርጫ ድረስ የአዲስአበባ ቀላል ባቡርን ስራ ለማስጀመር ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት የቻይና ኩባንያዎችን ጥብቅ መመሪያ የሰጠ ሲሆን ይህ ዓይነቱ የጥድፊያ አካሄድ በግንባታው ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ባለሙያዎች ከወዲሁ አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው፡፡
የአዲስአበባ ቀላል ባቡር ግንባታ በዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ ውስጥ የሌለና በእነአቶ መለስ ዜናዊ ደንገተኛ ውሳኔ የተጸነሰ ዕቅድ ሲሆን ግንባታው ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸውን የመንገድ መሰረተ ልማቶች፣ ሕንጻዎች እያፈራረስ ከመምጣቱም ባሻገር የባቡሩ መስመር ዝርጋታ ለእግረኞችና ለተሸከርካሪዎች ማቋረጫ ግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ እየተከናወነ መሆኑ በባለሙያዎች ጭምር ጠንካራ ትችትን አስከትሎአል፡፡
የመንግሥት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ እጅግ የተለጠጠ እና በፋይናንስና በሰውኃይል አቅም ሊተገበር እንደማይችል በተለይ በአገር ውስጥ በሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቶዎችና በውጪ አገር በሚገኙ ኢትጽያዊያን ባለሙያዎች በሰፊው ሲተች የቆየ ቢሆንም ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት ይህ የኒዮሊበራሊስቶች አፍራሽ አስተሳሰብ ነው በሚል ሲያጣጥለው ከመቆየቱም በላይ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር በፓርላማ ተቃዋሚዎችን በኃላ ዕቅዱ ሲሳካ እንዳታፍሩ እስከማለት መድረሳቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡